አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 10
10
የንጉሥ ሳኦል መሞት
(1ሳሙ. 31፥1-13)
1ፍልስጥኤማውያን መጥተው በእስራኤላውያን ላይ አደጋ ጣሉ፤ እስራኤላውያንም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ በዚያም ጦርነት በጊልቦዓ ተራራ ላይ ብዙ እስራኤላውያን ተገደሉ፤ 2ፍልስጥኤማውያን ግን ሳኦልንና ልጆቹን ተከታትለው ከሳኦል ልጆች ሦስቱን ዮናታንን፥ አቢናዳብንና ማልኪሹዓን ገደሉ፤ 3ሳኦል በነበረበት ግንባር ጦርነቱ እጅግ ተፋፍሞ ስለ ነበር ሳኦል በጠላት ፍላጻ ተመትቶ ክፉኛ ቈሰለ፤ 4እርሱም በዚህ ጊዜ ወጣት ጋሻ ጃግሬውን “እነዚህ አረማውያን መሳለቂያ እንዳያደርጉኝ ሰይፍህን መዘህ ግደለኝ” አለው፤ ወጣቱ ግን ይህን ለማድረግ እጅግ ስለ ፈራ አላደረገውም፤ ስለዚህም ሳኦል የራሱን ሰይፍ መዞ በመሬት ላይ በመትከል በላዩ ላይ ወደቀ፤ 5ወጣቱም የሳኦልን መሞት ባየ ጊዜ እርሱም የገዛ ሰይፉን በመሬት ላይ በመትከል በላዩ ላይ ወድቆ ሞተ። 6ስለዚህ ሳኦልና ሦስት ወንዶች ልጆቹ በአንድ ላይ ሞቱ፤ የመንግሥቱም ፍጻሜ ሆነ። 7በኢይዝራኤል በሸለቆው ይኖሩ የነበሩት እስራኤላውያን ሠራዊቱ እንደ ሸሸ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ በሰሙ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ከተሞቻቸውን ያዙ።
8በጦርነቱ ማግስት ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን እስራኤላውያን ለመግፈፍ በሄዱ ጊዜ የሳኦልና የልጆቹ ሬሳ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ተጋድሞ አገኙ፤ 9የሳኦልን ራስ ቈርጠው የጦር መሣሪያውን ከገፈፉ በኋላ በመልእክተኞች አስይዘው የምሥራቹን ለአማልክታቸውና ለሕዝባቸው ይነግሩላቸው ዘንድ ላኩአቸው። 10የሳኦልን የጦር መሣሪያዎች በአማልክታቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ አኖሩ፤ ራሱንም ዳጎን ተብሎ በሚጠራው አምላካቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ ሰቀሉት። 11በገለዓድ የሚገኘው የያቤሽ ሕዝብ፥ ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ የፈጸሙትን ግፍ በሰሙ ጊዜ፥ 12ኀያላን የሆኑ ሰዎች ሄደው የሳኦልንና የልጆቹን ሬሳ በመውሰድ ወደ ያቤሽ አመጡ፤ በዚያም በወርካ ዛፍ ሥር ከቀበሩአቸው በኋላ ሰባት ቀን በሙሉ ጾሙ።
13-14ሳኦል ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ባለመገኘቱ ምክንያት ሞተ፤ እርሱ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልፈጸመም፤ እንዲያውም የሙታን መናፍስት ጠሪዎችን በመጠየቅ መመሪያ ለማግኘት ሞከረ እንጂ እግዚአብሔርን አልጠየቀም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ገደለው፤ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አስተላለፈ። #ዘሌ. 19፥31፤ 20፥6፤ 1ሳሙ. 13፥8-14፤ 15፥1-24፤ 28፥7-8።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 10: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997