የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 18:1-17

ራእይ 18:1-17 NASV

ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም ነጸብራቅ የተነሣ ምድር በራች፤ እርሱም በብርቱ ድምፅ እንዲህ ብሎ ጮኸ፤ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! የአጋንንት መኖሪያ፣ የርኩሳን መናፍስት ሁሉ መጠጊያ፣ የርኩስና የአስጸያፊ ወፎች ሁሉ መጠለያ ሆነች። ሕዝቦች ሁሉ የዝሙቷን ቍጣ ወይን ጠጅ ጠጥተዋልና፤ የምድር ነገሥታት ከርሷ ጋራ አመንዝረዋል፤ የምድርም ነጋዴዎች ከብዙ ምቾቷ ኀይል የተነሣ በልጽገዋል።” ከዚያም ከሰማይ ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሕዝቤ ሆይ፤ በኀጢአቷ እንዳትተባበሩ፤ ከመቅሠፍቷም እንዳትካፈሉ፤ ከርሷ ውጡ፤ ኀጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ተከምሯልና፤ እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አስታውሷል። በሰጠችው መጠን ብድራቷን መልሱላት፤ ለሠራችው ሁሉ ዕጥፍ ክፈሏት፤ በቀላቀለችውም ጽዋ ዕጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት። ለራሷ ክብርና ምቾት የሰጠችውን ያህል፣ ሥቃይና ሐዘን ስጧት፤ በልቧም እንዲህ እያለች ትመካለች፤ ‘እንደ ንግሥት ተቀምጬአለሁ፤ መበለትም አይደለሁም፤ ከቶም አላዝንም፤’ ስለዚህ መቅሠፍቶቿ በአንድ ቀን ይመጡባታል፤ ሞት፣ ሐዘንና ራብ ይሆኑባታል፤ የሚፈርድባት ጌታ እግዚአብሔር ብርቱ ስለ ሆነ፣ በእሳት ትቃጠላለች። “ከርሷ ጋራ ያመነዘሩና በምቾት የኖሩ የምድር ነገሥታት፣ እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም። ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው እንዲህ ይላሉ፤ “ ‘አንቺ ታላቂቱ ከተማ ወዮልሽ! ወዮልሽ! አንቺ ባቢሎን ብርቱዪቱ ከተማ፣ ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ መጥቷል።’ “ጭነታቸውን ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ፣ የምድር ነጋዴዎችም ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉ፤ ጭነቱም፦ ወርቅ፣ ብር፣ የከበረ ድንጋይ፣ ዕንቍ፣ ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ፣ ሐምራዊ ልብስ፣ ሐር ልብስ፣ ቀይ ልብስ፣ መልካም ሽታ ያለው ዕንጨት ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ከውድ ዕንጨት፣ ከናስ፣ ከብረትና ከእብነ በረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፣ ቀረፋ፣ ቅመም፣ ከርቤ፣ ቅባት፣ ዕጣን፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የተሰለቀ ዱቄት፣ ስንዴ፣ ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ሠረገሎች፣ እንዲሁም ባሮችና የሰዎች ነፍሶች ነው። “እነርሱም፣ ‘የተመኘሽው ፍሬ ከአንቺ ርቋል፤ ብልጽግናሽና ክብርሽ ሁሉ ጠፍቷል፤ ዳግመኛም ተመልሶ አይመጣም’ ይላሉ። እነዚህን ነገሮች በመሸጥ በርሷ የበለጸጉ ነጋዴዎች ሥቃይዋን ፈርተው በሩቅ ይቆማሉ፤ እነርሱም ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም፤ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ ይላሉ፤ “ ‘ቀጭን የተልባ እግር፣ ሐምራዊና ቀይ ልብስ የለበሰች፣ በወርቅ፣ በከበረ ድንጋይና በዕንቍም ያጌጠች፣ ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ያ ሁሉ ሀብት በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፋ።’ “የመርከብ አዛዦች ሁሉ፣ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞች ሁሉ፣ የመርከብ ሠራተኞችና ኑሯቸውን በባሕር ላይ የመሠረቱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ።