ከዚህ በኋላ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩ ነጸብራቅ የተነሣ ምድር በራች፤ ከፍ ባለ ድምፅም እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! የአጋንንት መኖሪያ ሆነች! የርኩሳን መናፍስት ማደሪያ ሆነች! የሚያጸይፉና የሚያስጠሉ ወፎች መጠለያ ሆነች! የሚያሰክረውን የአመንዝራነትዋን ወይን ጠጅ ለሕዝቦች ሁሉ አጠጥታለች፤ የምድር ነገሥታት ከእርስዋ ጋር አመንዝረዋል፤ የምድር ነጋዴዎችም ከብዙ ምቾትዋ የተነሣ ሀብታሞች ሆነዋል።” ሌላ ድምፅም ከሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሕዝቤ ሆይ! በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ፤ የመቅሠፍትዋም ተካፋዮች እንዳትሆኑ፤ ከእርስዋ ውጡ! የኃጢአትዋ ክምር እስከ ሰማይ ደርሶአል፤ እግዚአብሔር በደሎችዋን አስታውሶአል፤ በሰጠችው መጠን ስጥዋት፤ ባደረገችውም ሥራ እጥፍ ክፈልዋት፤ እርስዋ ልዩ ልዩ መጠጦችን በቀላቀለችበት ጽዋ ውስጥ እጥፍ ኀይለኛ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ እርስዋ ለራስዋ ክብርንና ምቾትን የሰጠችውን ያኽል ሥቃይና ሐዘን ስጡአት፤ እርስዋ በልብዋ ‘እንደ ንግሥት ተቀምጬአለሁ፤ መበለትም አይደለሁም፤ ሐዘንም ከቶ አይደርስብኝም’ በማለት ትመካለች። ስለዚህ መቅሠፍቶችዋ ሁሉ በአንድ ቀን ይደርሱባታል፤ ሞትና ሐዘን ራብም ይደርሱባታል፤ በእሳትም ትቃጠላለች፤ በእርስዋ ላይ የሚፈርድባት ጌታ አምላክ ብርቱ ነው።” ከእርስዋ ጋር ያመነዘሩና በምቾት የኖሩ የምድር ነገሥታት እርስዋ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው “አንቺ ታላቂቱ ከተማ፥ አንቺ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን ሆይ! ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስለ መጣ፥ ወዮልሽ! ወዮልሽ!” ይላሉ። የመርከባቸውን ጭነት ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ የምድር ነጋዴዎችም ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላታልም፤ በመርከባቸው የተጫነውም ወርቅ፥ ብር፥ የከበረ ድንጋይ፥ ዕንቊ፥ ቀጭን ልብስ፥ ሐምራዊ ልብስ፥ ሐር ልብስ፥ ቀይ ልብስና መልካም መዓዛ ያለው እንጨት ሁሉ፥ ከዝኆን ጥርስ፥ ውድ ከሆነ እንጨት፥ ከነሐስ፥ ከብረትና ከእብነበረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋ፥ ቅመም፥ የሚሸት እንጨት፥ ከርቤ፥ ዕጣን፥ ወይን ጠጅ፥ የወይራ ዘይት፥ ዱቄት፥ ስንዴ፥ ከብቶች፥ በጎች፥ ፈረሶች፥ ሠረገላዎች፥ ባርያዎችና ሌሎችም ሰዎች ናቸው። ነጋዴዎቹም “አንቺ የተመኘሻቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ከአንቺ ርቀው ሄደዋል፤ ሀብትሽም ጌጣ ጌጥሽም ሁሉ ጠፍቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ እነዚህን ሁሉ ከቶ አታገኚአቸውም!” ይሉአታል። እነዚህን ነገሮች ሁሉ እየገዙ ሀብታሞች የሆኑ ነጋዴዎች ሥቃይዋን በመፍራት በሩቅ ይቆማሉ፤ እያለቀሱና እያዘኑም፥ “ቀጭን ልብስና ሐምራዊ ልብስ ቀይ ልብስም ትለብስ የነበረች፥ በወርቅና በከበረ ድንጋይ በዕንቊም ታሸበርቅ የነበረች፤ ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ያን ያኽል ሀብት በአንድ ሰዓት ጠፋ!” ይላሉ። የመርከብ አዛዦች ሁሉ፥ በመርከብ የሚጓዙ ሰዎች ሁሉ፥ በመርከብ ላይ የሚሠሩ ሁሉ፥ በባሕር ላይ የሚነግዱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ፤
የዮሐንስ ራእይ 18 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ራእይ 18:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos