ራእይ 17:3-14

ራእይ 17:3-14 NASV

ቀጥሎም መልአኩ በመንፈስ ወደ በረሓ ወሰደኝ፤ በዚያም አንዲት ሴት በስድብ ስሞች በተሞላ፣ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ባሉት ቀይ አውሬ ላይ ተቀምጣ አየሁ። ሴቲቱም ሐምራዊና ቀይ ልብስ ተጐናጽፋ ነበር፤ ደግሞም በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቈችም አጊጣ ነበር፤ በእጇም የሚያስጸይፍ ነገርና የዝሙቷ ርኩሰት የሞላበትን የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር። በግንባሯም ላይ እንዲህ የሚል የምስጢር ስም ተጽፎ ነበር፤ ታላቂቱ ባቢሎን፣ የአመንዝሮችና የምድር ርኩሰቶች እናት። ሴቲቱንም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ እጅግ ተደነቅሁ። ከዚያም መልአኩ እንዲህ አለኝ፤ የምትደነቀው ለምንድን ነው? የሴቲቱን፣ እርሷ የተቀመጠችበትንም፣ እንዲሁም ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እነግርሃለሁ። ያየኸው አውሬ ቀደም ሲል ነበረ፤ አሁን ግን የለም፤ በኋላም ከጥልቁ ጕድጓድ ይወጣል፤ ወደ ጥፋቱም ይሄዳል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ የምድር ነዋሪዎች አውሬው ቀድሞ የነበረ፣ አሁን ግን የሌለ፣ በኋላም የሚመጣ መሆኑን ሲያዩ ይደነቃሉ። “ይህም፣ ጥበብ ያለው አእምሮ ይጠይቃል። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የምትቀመጥባቸው ሰባት ተራሮች ናቸው፤ እነርሱም ደግሞ ሰባት ነገሥታት ናቸው። ዐምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አለ፤ ሌላውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣ ግን ሊቈይ የሚገባው ለጥቂት ጊዜ ነው። ቀድሞ የነበረውና አሁን የሌለው አውሬ ስምንተኛው ንጉሥ ነው፤ እርሱም ከሰባቱ አንዱ ሲሆን ወደ ጥፋቱ ይሄዳል። “ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ፣ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ነገር ግን ከአውሬው ጋራ ለአንድ ሰዓት እንዲነግሡ ሥልጣን ይቀበላሉ። አንድ ሐሳብም አላቸው፤ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ፤ እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉ ግን ድል ይነሣቸዋል፤ ምክንያቱም እርሱ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ነው፤ ከርሱ ጋራ ያሉ የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም ዐብረው ድል ይነሣሉ።”