ከዚህ በኋላ መልአኩ በመንፈስ ወደ በረሓ ወሰደኝ፤ በሁለንተናው የስድብ ስሞች በተጻፉት፥ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ባሉት በቀይ አውሬ ላይ የተቀመጠች አንዲት ሴት አየሁ። ሴቲቱ ሐምራዊና ቀይ ልብስ ለብሳ ነበር፤ በወርቅና በከበረ ድንጋይ በዕንቆችም አሸብርቃ ነበር፤ በእጅዋም የሚያጸይፍ ነገርና የአመንዝራነትዋ ርኲሰት የሞላበትን የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር። በግንባርዋም ላይ “የአመንዝሮችና የምድር ርኲሰቶች እናት፥ ታላቂቱ ባቢሎን” የሚል ምሥጢር ስም ተጽፎ ነበር። ያቺ ሴት በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ሰማዕታት ደም ሰክራ አየኋት፤ ባየኋትም ጊዜ እጅግ በጣም ተደነቅሁ። መልአኩ ግን እንዲህ አለኝ፤ “ስለምን ትደነቃለህ? የሴቲቱን ምሥጢርና እርስዋ የተቀመጠችበትን፥ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ያሉትን፥ የአውሬውን ምሥጢር እገልጥልሃለሁ፤ ያየኸው አውሬ ቀድሞ ነበር፤ አሁን የለም፤ በኋላ ከጥልቁ ጒድጓድ ይወጣል፤ ወደ ጥፋቱም ይሄዳል፤ ዓለም ሲፈጠር ጀምሮ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ የምድር ኗሪዎች፥ አውሬው ቀድሞ የነበረ፥ አሁን የሌለ፥ በኋላ የሚመጣ መሆኑን ሲያዩ ይደነቃሉ። “ጥበብ ያለው አእምሮ የሚፈለገው እዚህ ላይ ነው፤ ሰባቱ ራሶች፥ ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፤ እንዲሁም ሰባት ነገሥታት ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አሁን አለ፤ ሌላው ገና አልመጣም፤ እርሱ ሲመጣ ለጥቂት ጊዜ ብቻ መቈየት አለበት። ስምንተኛው ንጉሥ ቀድሞ የነበረውና አሁን የሌለው አውሬ ነው፤ እርሱ ከሰባቱ አንዱ ነው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። “ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች ገና ያልነገሡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ነገር ግን ለአንዲት ሰዓት ከአውሬው ጋር እንዲነግሡ የመንገሥ ሥልጣን ያገኛሉ። እነዚህ ዐሥር ነገሥታት አንድ ሐሳብ አላቸው፤ እነርሱ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውን ለአውሬው ያስረክባሉ፤ እነርሱ በበጉ ላይ ጦርነት ይከፍታሉ፤ ነገር ግን በጉ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ ድል ይነሣቸዋል፤ ከእርሱ ጋር ያሉት የተጠሩ የተመረጡና የታመኑ ናቸው።”
የዮሐንስ ራእይ 17 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ራእይ 17:3-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች