የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 78:34-55

መዝሙር 78:34-55 NASV

እርሱ በገደላቸው ጊዜ ፈለጉት፤ ከልባቸው በመሻትም ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ። እግዚአብሔር ዐለታቸው፣ ልዑል አምላክ ቤዛቸው እንደ ሆነ ዐሰቡ። ነገር ግን በአፋቸው ሸነገሉት፤ በአንደበታቸው ዋሹት። ልባቸው በርሱ የጸና አልነበረም፤ ለኪዳኑም ታማኞች አልነበሩም። እርሱ ግን መሓሪ እንደ መሆኑ፣ በደላቸውን ይቅር አለ፤ አላጠፋቸውም፤ ቍጣውን ብዙ ጊዜ ገታ፤ መዓቱንም ሁሉ አላወረደም። ወጥቶ የማይመለስ ነፋስ፣ ሥጋ ለባሾች መሆናቸውን ዐሰበ። በምድረ በዳ ስንት ጊዜ ዐመፁበት! በበረሓስ ምን ያህል አሳዘኑት! ደግመው ደጋግመው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አስቈጡት። እነርሱን በዚያ ቀን ከጠላት የታደገበትን፣ ያን ኀይሉን አላስታወሱም፤ በግብጽ ያደረገውን ታምራዊ ምልክት፣ በጣኔዎስም በረሓ ያሳየውን ድንቅ ሥራ አላሰቡም። ወንዞቻቸውን ወደ ደም ለወጠ፤ ከጅረቶቻቸውም መጠጣት አልቻሉም። የዝንብ ሰራዊት ሰደደባቸው፤ ነደፏቸውም፤ ጓጕንቸርም ላከባቸው፤ ሰዎችንም አጠፉ። አዝመራቸውን ለኵብኵባ፣ ሰብላቸውንም ለአንበጣ ሰጠባቸው። የወይን ተክላቸውን በበረዶ፣ የበለስ ዛፋቸውንም በውርጭ አጠፋ። ከብቶቻቸውን ለበረዶ፣ የከብት መንጋቸውን ለመብረቅ እሳት ዳረገ። ጽኑ ቍጣውን በላያቸው ሰደደ፤ መዓቱን፣ የቅናቱን ቍጣና መቅሠፍቱን ላከባቸው፤ አጥፊ የመላእክት ሰራዊትም ሰደደባቸው። ለቍጣው መንገድ አዘጋጀ፤ ነፍሳቸውንም ከሞት አላተረፈም፤ ነገር ግን ሕይወታቸውን ለመቅሠፍት አሳልፎ ሰጠ። የዐፍላ ጕልበታቸው መጀመሪያ የሆኑትን በካም ድንኳን፣ በኵሮቻቸውንም ሁሉ በግብጽ ምድር ፈጀ። ሕዝቡን ግን እንደ በግ አወጣቸው፤ በምድረ በዳም እንደ መንጋ መራቸው። ያለ ሥጋት መራቸው፤ እነርሱም አልፈሩም፤ ጠላቶቻቸውን ግን ባሕር ዋጣቸው። ቀኝ እጁም ወዳስገኘችው ወደዚህ ተራራ፣ ወደ ቅድስት ምድር አገባቸው። ሕዝቦችን ከፊታቸው አባረረ፤ ምድራቸውን ርስት አድርጎ በገመድ አከፋፈላቸው፤ የእስራኤልንም ነገዶች በጠላቶቻቸው ቤት አኖረ።