መዝሙር 78
78
መዝሙር 78
በእስራኤል የተገኘ ታሪክ
የአሳፍ ትምህርት።
1ሕዝቤ ሆይ፤ ትምህርቴን ስማ፤
ጆሮህንም ወደ አንደበቴ ቃል አዘንብል።
2አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤
ከጥንት በነበረ እንቈቅልሽ እናገራለሁ፤
3ይህም የሰማነውና ያወቅነው፣
አባቶቻችንም የነገሩን ነው።
4እኛም ከልጆቻቸው አንደብቀውም፤
የእግዚአብሔርን ምስጋና፣
ኀይሉንና ያደረገውን ድንቅ ሥራ፣
ለሚቀጥለው ትውልድ እንናገራለን።
5ለያዕቆብ ሥርዐትን መሠረተ፤
በእስራኤልም ሕግን ደነገገ፤
ልጆቻቸውንም እንዲያስተምሩ፣
አባቶቻችንን አዘዘ።
6ይህም የሚቀጥለው ትውልድ እንዲያውቅ፣
እነርሱም በተራቸው ለልጆቻቸው፣
ገና ለሚወለዱትም እንዲነግሩ ነው።
7እነርሱም በእግዚአብሔር ይታመናሉ፤
የእርሱንም ሥራ አይረሱም፤
ትእዛዞቹንም ይጠብቃሉ።
8ነገር ግን እንደ አባቶቻቸው፣
እልኸኞችና ዐመፀኞች፣
ልቡን ያላቀና፣
መንፈሱም በእግዚአብሔር የማይታመን ትውልድ አይሆኑም።
9የኤፍሬም ልጆች የታጠቁ ቀስተኞች ቢሆኑም፣
በጦርነት ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ።
10የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፤ በሕጉም መሠረት ለመሄድ እንቢ አሉ።
11እርሱ የሠራውን ሥራ፣
ያሳያቸውንም ድንቅ ነገር ረሱ።
12አባቶቻቸው በዐይናቸው እያዩ፣
በግብፅ አገር፣ በጣኔዎስ ምድር ታምራት አደረገ።
13ባሕሩን ከፍሎ አሻገራቸው፤
ውሃውንም እንደ ክምር አቆመ።
14ቀን በደመና መራቸው፤
ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን።
15ዐለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፤
እንደ ባሕር የበዛ ውሃ አጠጣቸው፤
16ምንጭ ከቋጥኝ አፈለቀ፤
ውሃን እንደ ወንዝ አወረደ።
17እነርሱ ግን በምድረ በዳ በልዑል ላይ በማመፅ፣
በእርሱ ላይ ኀጢአት መሥራታቸውን ቀጠሉ።
18እጅግ የተመኙትን ምግብ በመጠየቅ፣
እግዚአብሔርን በልባቸው ተፈታተኑት።
19እንዲህም ብለው በእግዚአብሔር ላይ ተናገሩ፤
“እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማእድ ማሰናዳት ይችላልን?
20ዐለቱን ሲመታ፣ ውሃ ተንዶለዶለ፤
ጅረቶችም ጐረፉ፤
ታዲያ፣ እንጀራንም መስጠት ይችላል?
ሥጋንስ ለሕዝቡ ሊያቀርብ ይችላል?”
21 እግዚአብሔር ይህን ሲሰማ፣ እጅግ ተቈጣ፤
በያዕቆብም ላይ እሳት ነደደ፤
ቍጣውም በእስራኤል ላይ ተነሣ፤
22በእግዚአብሔር አላመኑምና፤
በእርሱም ማዳን አልታመኑም።
23እርሱ ግን ከላይ ደመናትን አዘዘ፤
የሰማይንም ደጆች ከፈተ፤
24ይበሉም ዘንድ መና አዘነበላቸው፤
የሰማይንም መብል ሰጣቸው።
25ሰዎች የመላእክትን እንጀራ በሉ፤
ጠግበው እስከሚተርፍ ድረስ ምግብ ላከላቸው።
26የምሥራቁን ነፋስ ከሰማይ አስነሣ፤
የደቡብንም ነፋስ በኀይሉ አመጣ።
27ሥጋን እንደ ዐፈር፣
የሚበሩትን ወፎች እንደ ባሕር አሸዋ አዘነበላቸው፤
28በሰፈራቸውም ውስጥ፣
በድንኳናቸው ዙሪያ አወረደ።
29እነርሱም እስኪጠግቡ ድረስ በሉ፤
እጅግ የጐመጁትን ሰጥቷቸዋልና።
30ነገር ግን ገና ምኞታቸውን ሳያረኩ፣
ምግቡ ገና በአፋቸው ውስጥ እያለ፣
31የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው ላይ መጣ፤
ከመካከላቸውም ብርቱ ነን ባዮችን ገደለ፤
የእስራኤልንም አበባ ወጣቶች ቀጠፈ።
32ይህም ሁሉ ሆኖ በበደላቸው ገፉበት፤
ድንቅ ሥራዎቹንም አላመኑም።
33ስለዚህ ዘመናቸውን በከንቱ፣
ዕድሜያቸውንም በድንጋጤ ጨረሰ።
34እርሱ በገደላቸው ጊዜ ፈለጉት፤
ከልባቸው በመሻትም ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ።
35እግዚአብሔር ዐለታቸው፣
ልዑል አምላክ ቤዛቸው እንደ ሆነ ዐሰቡ።
36ነገር ግን በአፋቸው ሸነገሉት፤
በአንደበታቸው ዋሹት።
37ልባቸው በእርሱ የጸና አልነበረም፤
ለኪዳኑም ታማኞች አልነበሩም።
38እርሱ ግን መሓሪ እንደ መሆኑ፣
በደላቸውን ይቅር አለ፤
አላጠፋቸውም፤
ቍጣውን ብዙ ጊዜ ገታ፤
መዓቱንም ሁሉ አላወረደም።
39ወጥቶ የማይመለስ ነፋስ፣
ሥጋ ለባሾች መሆናቸውን ዐሰበ።
40በምድረ በዳ ስንት ጊዜ ዐመፁበት!
በበረሓስ ምን ያህል አሳዘኑት!
41ደግመው ደጋግመው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤
የእስራኤልንም ቅዱስ አስቈጡት።
42እነርሱን በዚያን ቀን ከጠላት የታደገበትን፣
ያን ኀይሉን አላስታወሱም፤
43በግብፅ ያደረገውን ታምራዊ ምልክት፣
በጣኔዎስም በረሓ ያሳየውን ድንቅ ሥራ አላሰቡም።
44ወንዞቻቸውን ወደ ደም ለወጠ፤
ከጅረቶቻቸውም መጠጣት አልቻሉም።
45የዝንብ ሰራዊት ሰደደባቸው፤ ነደፏቸውም፤
ጓጕንቸርም ላከባቸው፤ ሰዎችንም አጠፉ።
46አዝመራቸውን ለኵብኵባ፣
ሰብላቸውንም ለአንበጣ ሰጠባቸው።
47የወይን ተክላቸውን በበረዶ፣
የበለስ ዛፋቸውንም በውርጭ አጠፋ።
48ከብቶቻቸውን ለበረዶ፣
የከብት መንጋቸውን ለመብረቅ እሳት ዳረገ።
49ጽኑ ቍጣውን በላያቸው ሰደደ፤
መዓቱን፣ የቅናቱን ቍጣና
መቅሠፍቱን ላከባቸው፤
አጥፊ የመላእክት ሰራዊትም ሰደደባቸው።
50ለቍጣው መንገድ አዘጋጀ፤
ነፍሳቸውንም ከሞት አላተረፈም፤
ነገር ግን ሕይወታቸውን ለመቅሠፍት አሳልፎ ሰጠ።
51የዐፍላ ጕልበታቸው መጀመሪያ የሆኑትን በካም ድንኳን፣
በኵሮቻቸውንም ሁሉ በግብፅ ምድር ፈጀ።
52ሕዝቡን ግን እንደ በግ አወጣቸው፤
በምድረ በዳም እንደ መንጋ መራቸው።
53በሰላም መራቸው፤ እነርሱም አልፈሩም፤
ጠላቶቻቸውን ግን ባሕር ዋጣቸው።
54ቀኝ እጁም ወዳስገኘችው ወደዚህ ተራራ፣
ወደ ቅድስት ምድር አገባቸው።
55ሕዝቦችን ከፊታቸው አባረረ፤
ምድራቸውን ርስት አድርጎ አከፋፈላቸው፤
የእስራኤልንም ነገዶች በጠላቶቻቸው ቤት አኖረ።
56እነርሱ ግን አምላክን ተፈታተኑት፤
በልዑልም ላይ ዐመፁ፤
ሥርዐቱንም አልጠበቁም።
57ተመልሰው እንደ አባቶቻቸው ከዳተኛ ሆኑ፤
እንደማያስተማምን ጠማማ ቀስት ተወላገዱ።
58በኰረብታ ማምለኪያዎቻቸው አስቈጡት፤
ተቀርጸው በተሠሩ ጣዖቶቻቸው አስቀኑት።
59እግዚአብሔር ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤
እስራኤልንም ፈጽሞ ተወ።
60በሰዎች መካከል ያቆማትን ድንኳን፣
የሴሎን ማደሪያ ተዋት።
61የኀይሉን ምልክት አስማረካት፤
ክብሩንም ለጠላቶቹ እጅ አሳልፎ ሰጠ።
62ሕዝቡን ለሰይፍ ዳረገ፤
በርስቱም ላይ እጅግ ተቈጣ።
63ጕልማሶቻቸውን እሳት በላቸው፤
ልጃገረዶቻቸውም የሰርግ ዘፈን አልተዘፈነላቸውም።
64ካህናታቸው በሰይፍ ተገደሉ፤
መበለቶቻቸውም ማልቀስ ተሳናቸው።
65ጌታም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤
የወይን ጠጅ ስካር እንደ በረደለት ጀግናም ብድግ አለ።
66ጠላቶቹን መትቶ ወደ ኋላ መለሳቸው፤
የዘላለም ውርደትም አከናነባቸው።
67የዮሴፍን ድንኳን ተዋት፤
የኤፍሬምንም ነገድ አልመረጠም።
68ነገር ግን የይሁዳን ነገድ፣
የወደዳትን የጽዮንን ተራራ መረጠ።
69መቅደሱን እንደ ታላቅ ከፍታ፣
ለዘላለም እንደ መሠረታት ምድር ሠራት።
70ባሪያውን ዳዊትን መረጠ፤
ከበጎች ጕረኖ ውስጥ ወሰደው፤
71ለሕዝቡ ለያዕቆብ፣
ለርስቱም ለእስራኤል እረኛ ይሆን ዘንድ፣
የሚያጠቡ በጎችን ከመከተል አመጣው።
72እርሱም በቅን ልቡ ጠበቃቸው፤
ብልኀት በተሞላ እጁም መራቸው።
Currently Selected:
መዝሙር 78: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.