የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 78:34-55

መጽሐፈ መዝሙር 78:34-55 አማ05

ከእነርሱ ጥቂቶቹን በሞት በቀጣበት ጊዜ የቀሩት ወደ እርሱ ይመለሱ ጀመር፤ ንስሓ ገብተውም ወደ እርሱ ከልባቸው ይመለሳሉ። እግዚአብሔር አምባቸው እንደ ሆነ ያስታውሳሉ፤ ልዑል እግዚአብሔርም አዳኛቸው እንደ ሆነ ያስባሉ። ነገር ግን በቃላቸው ሸነገሉት፤ የሚናገሩትም ሁሉ ሐሰት ነበር። ለእርሱ ታማኞች አልነበሩም፤ የእርሱንም ቃል ኪዳን አላከበሩም። ሆኖም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ምሕረትን አደረገ፤ ኃጢአታቸውን ይቅር አላቸው እንጂ አላጠፋቸውም። ብዙ ጊዜ ቊጣውን መለሰ፤ ብዙ ጊዜም መዓቱን ገታ። ካለፈ በኋላ እንደማይመለስ ነፋስ፥ ሟች ፍጥረቶች መሆናቸውን አስታወሰ። በበረሓ ሳሉ ብዙ ጊዜ በእርሱ ላይ ዐመፁ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ አሳዘኑት። በመደጋገም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት። እነርሱን ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀንና ታላቅ ኀይሉን አላስታወሱም። በግብጽ አገር በጾዓን ሜዳ ያደረጋቸውን ታላላቅ ሥራዎችና ተአምራቱን ዘነጉ። የወንዞቻቸውን ውሃ ወደ ደም ለወጠ፤ ስለዚህ ግብጻውያን ከወንዞቻቸው ውሃ መጠጣት አልቻሉም። እነርሱን የሚያሠቃዩ ዝንቦችንና ጥፋትን የሚያስከትሉ እንቊራሪቶችን ወደ እነርሱ ላከ። ሰብላቸውን ለኩብኩባ፥ ምርታቸውንም ለአንበጣ ሰጠ። የወይን ተክሎቻቸውን በበረዶ፥ የበለስ ዛፎቻቸውንም በውርጭ አጠፋ። ከብቶቻቸውን በበረዶ፥ በጎቻቸውንም በመብረቅ ገደለ። የጥፋት መልእክተኞች ቡድን የሆኑትን አስፈሪውንና ኀይለኛ ቊጣውን፥ ማዋረዱንና ማስጨነቁን ላከባቸው። ለቊጣው መንገድን አዘጋጀ፤ ከሞትም አላዳናቸውም፤ ነገር ግን ለመቅሠፍት አሳልፎ ሰጣቸው። የካምን ልጆች የመጀመሪያ የወንድነት ፍሬ፥ በግብጽ በኲሮችን ሁሉ ገደለ። ሕዝቡን አውጥቶ እንደ በጎች አሰማራቸው፤ በበረሓም እንደ በግ መንጋ መራቸው። በሰላም ስለ መራቸው አልፈሩም፤ ነገር ግን ባሕሩ ተጥለቅልቆ ጠላቶቻቸውን አሰጠማቸው። ወደ ተቀደሰችው ምድሩ፥ በኀይሉ ወደያዛት ወደ ተራራማዋ አገር አመጣቸው። ከእነርሱ በፊት አሕዛብን አባረረ፤ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ለእስራኤል ነገዶች አከፋፈለ፤ ቤቶቻቸውንም ለራሱ ሕዝብ ሰጠ።