ዘኍልቍ 10:29-36

ዘኍልቍ 10:29-36 NASV

በዚህ ጊዜ ሙሴ የሚስቱን አባት የምድያማዊውን የራጉኤልን ልጅ ኦባብን፣ “እነሆ፤ እግዚአብሔር፣ ‘እሰጣችኋለሁ’ ወዳለን ምድር ጕዞ ጀምረናል፤ በመልካም ሁኔታ ስለምናኖርህ ከእኛ ጋራ ሂድ፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል በጎ ነገር ለማድረግ ቃል ገብቷልና አለው።” እርሱም መልሶ፣ “ይህስ አይሆንም፤ አልሄድም፤ ወደ አገሬና ወደ ወገኖቼ ተመልሼ እሄዳለሁ” አለው። ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እባክህ አትለየን፤ በምድር በዳ ውስጥ የት መስፈር እንደሚገባን አንተ ታውቃለህ፤ ዐይናችንም ትሆናለህ። ከእኛ ጋራ ብትሄድ እግዚአብሔር ከሚያደርግልን መልካም ነገር ሁሉ እኛም እናደርግልሃለን።” ስለዚህ ከእግዚአብሔር ተራራ ተነሥተው የሦስት ቀን መንገድ ተጓዙ፤ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦትም በእነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ የሚያርፉበትን ቦታ በመፈለግ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር። ከሰፈራቸው በሚነሡበት ጊዜ የእግዚአብሔር ደመና ቀን ቀን ከላያቸው ነበር። ታቦቱ ለጕዞ በተነሣ ጊዜ ሁሉ ሙሴ፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ተነሥ! ጠላቶችህ ይበተኑ፤ የሚጠሉህም ከፊትህ ይሽሹ” ይል ነበር። ባረፉ ጊዜም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በብዙ ሺሕ ወደሚቈጠሩት እስራኤላውያን ተመለስ” ይል ነበር።