በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ ከፍ ባለ ድምፅ ለሕዝቡ አነበቡ፤ አሞናዊም ሆነ ሞዓባዊ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ፈጽሞ እንዳይገባ የሚከለክል ተጽፎ ተገኘ፤ ይህ የሆነው እስራኤልን በምግብና ውሃ መስተንግዶ በመቀበል ፈንታ፣ በለዓም እንዲረግምላቸው በገንዘብ ስለ ገዙት ነበር። ይሁን እንጂ አምላካችን ርግማኑን ወደ በረከት ለወጠው። ሕዝቡም ይህን ሕግ በሰሙ ጊዜ፣ የባዕድ ወገን የሆኑትን ሁሉ ከእስራኤል ለዩ። ቀድሞ የአምላካችን ዕቃ ቤቶች ኀላፊ ሆኖ የተሾመው ካህኑ ኤልያሴብ ነበር፤ እርሱም ከጦቢያ ጋራ የጠበቀ ወዳጅነት ነበረው፤ ከዚህ በፊት የእህል ቍርባኑ፣ ዕጣኑ፣ የቤተ መቅደሱ ዕቃዎች፣ የእህሉ ዐሥራትና፣ ለሌዋውያን፣ ለመዘምራንና ለበር ጠባቂዎች የታዘዘው አዲሱ ወይንና ዘይት፣ ለካህናቱም የሚመጣው ስጦታ ይቀመጥበት የነበረውን ትልቁን የዕቃ ቤት እንዲኖርበት ሰጥቶት ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን እኔ በኢየሩሳሌም አልነበርሁም፤ ምክንያቱም በባቢሎን ንጉሥ በአርጤክስስ ሠላሳ ሁለተኛ ዓመት ተመልሼ ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበር። ከጥቂት ጊዜም በኋላ የንጉሡን ፈቃድ ጠይቄ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለስሁ፤ በዚያም ኤልያሴብ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦቢያ አንድ መኖሪያ ክፍል በመስጠት የፈጸመውን ክፉ ድርጊት ተረዳሁ። እኔም በጣም ዐዘንሁ፤ የጦቢያንም የቤት ዕቃ ሁሉ ከክፍሉ እያወጣሁ ወደ ውጭ ጣልሁ። ክፍሎቹንም እንዲያነጹ ትእዛዝ ሰጠሁ፤ ከዚያም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች፣ የእህሉን ቍርባንና ዕጣኑን ጭምር መልሼ አስገባሁ። እንዲሁም ለሌዋውያን የተመደበው ድርሻ እንዳልተሰጣቸውና አገልግሎቱን በኀላፊነት የሚመሩ ሌዋውያንና መዘምራን ሁሉ ወደየርስታቸው መመለሳቸውን ተረዳሁ። ስለዚህ ሹማምቱን ገሥጬ፣ “ቤተ መቅደሱ እስከዚህ ቸል የተባለው ለምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅኋቸው። ከዚያም እነርሱን በአንድነት ሰብስቤ ወደ ምድብ ሥራቸው እንዲመለሱ አደረግሁ። ይሁዳም ሁሉ የእህሉን፣ የአዲሱን ወይንና የዘይቱን ዐሥራት ወደ ዕቃ ቤቶቹ አስገቡ። ለዕቃ ቤቶቹም ካህኑን ሰሌምያን፣ ጸሓፊውን ሳዶቅንና ፈዳያ የተባለውን ሌዋዊ ኀላፊ አድርጌ ሾምሁ፤ መደብሁ፤ እንዲሁም የመታንያን ልጅ፣ የዛኩርን ልጅ ሐናንን ረዳታቸው አደረግሁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ታማኞች ነበሩ። ሥራቸውም ለወንድሞቻቸው የተመደበውን ቀለብ ማከፋፈል ነበረ። አምላኬ ሆይ፤ ስለዚህ ነገር አስበኝ፤ ለአምላኬ ቤትና ለአገልግሎቱ ስል በታማኝነት ያከናወንሁትን አታጥፋ።
ነህምያ 13 ያንብቡ
ያዳምጡ ነህምያ 13
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ነህምያ 13:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች