ነህምያ 13
13
ነህምያ በመጨረሻ የወሰደው የተሐድሶ ርምጃ
1በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ ከፍ ባለ ድምፅ ለሕዝቡ አነበቡ፤ አሞናዊም ሆነ ሞዓባዊ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ፈጽሞ እንዳይገባ የሚከለክል ተጽፎ ተገኘ፤ 2ይህ የሆነው እስራኤልን በምግብና ውሃ መስተንግዶ በመቀበል ፈንታ፣ በለዓም እንዲረግምላቸው በገንዘብ ስለ ገዙት ነበር። ይሁን እንጂ አምላካችን ርግማኑን ወደ በረከት ለወጠው። 3ሕዝቡም ይህን ሕግ በሰሙ ጊዜ፣ የባዕድ ወገን የሆኑትን ሁሉ ከእስራኤል ለዩ።
4ቀድሞ የአምላካችን ዕቃ ቤቶች ኀላፊ ሆኖ የተሾመው ካህኑ ኤልያሴብ ነበር፤ እርሱም ከጦብያ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበረው፤ 5ከዚህ በፊት የእህል ቍርባኑ፣ ዕጣኑ፣ የቤተ መቅደሱ ዕቃዎች፣ የእህሉ ዐሥራትና፣ ለሌዋውያን፣ ለመዘምራንና ለበር ጠባቂዎች የታዘዘው አዲሱ ወይንና ዘይት፣ ለካህናቱም የሚመጣው ስጦታ ይቀመጥበት የነበረውን ትልቁን የዕቃ ቤት እንዲኖርበት ሰጥቶት ነበር።
6ይህ ሁሉ ሲሆን እኔ በኢየሩሳሌም አልነበርሁም፤ ምክንያቱም በባቢሎን ንጉሥ በአርጤክስስ ሠላሳ ሁለተኛ ዓመት ተመልሼ ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበር። ከጥቂት ጊዜም በኋላ የንጉሡን ፈቃድ ጠይቄ 7ወደ ኢየሩሳሌም ተመለስሁ፤ በዚያም ኤልያሴብ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦብያ አንድ መኖሪያ ክፍል በመስጠት የፈጸመውን ክፉ ድርጊት ተረዳሁ። 8እኔም በጣም ዐዘንሁ፤ የጦብያንም የቤት ዕቃ ሁሉ ከክፍሉ እያወጣሁ ወደ ውጭ ጣልሁ። 9ክፍሎቹንም እንዲያነጹ ትእዛዝ ሰጠሁ፤ ከዚያም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች፣ የእህሉን ቍርባንና ዕጣኑን ጭምር መልሼ አስገባሁ።
10እንዲሁም ለሌዋውያን የተመደበው ድርሻ እንዳልተሰጣቸውና አገልግሎቱን በኀላፊነት የሚመሩ ሌዋውያንና መዘምራን ሁሉ ወደየርስታቸው መመለሳቸውን ተረዳሁ። 11ስለዚህ ሹማምቱን ገሥጬ፣ “ቤተ መቅደሱ እስከዚህ ቸል የተባለው ለምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅኋቸው። ከዚያም እነርሱን በአንድነት ሰብስቤ ወደ ምድብ ሥራቸው እንዲመለሱ አደረግሁ።
12ይሁዳም ሁሉ የእህሉን፣ የአዲሱን ወይንና የዘይቱን ዐሥራት ወደ ዕቃ ቤቶቹ አስገቡ። 13ለዕቃ ቤቶቹም ካህኑን ሰሌምያን፣ ጸሓፊውን ሳዶቅንና ፈዳያ የተባለውን ሌዋዊ ኀላፊ አድርጌ ሾምሁ፤ መደብሁ፤ እንዲሁም የመታንያን ልጅ፣ የዘኩርን ልጅ ሐናንን ረዳታቸው አደረግሁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ታማኞች ነበሩ። ሥራቸውም ለወንድሞቻቸው የተመደበውን ቀለብ ማከፋፈል ነበረ።
14አምላኬ ሆይ፤ ስለዚህ ነገር አስበኝ፤ ለአምላኬ ቤትና ለአገልግሎቱ ስል በታማኝነት ያከናወንሁትን አታጥፋ።
15በእነዚያ ቀናት በይሁዳ በሰንበት ቀን የወይን መጭመቂያ የሚረግጡ፣ እህል የሚያስገቡና፣ የወይን ጠጅ፣ የወይን ዘለላ፣ የበለስና ሌሎችን የጭነት ዐይነቶች ሁሉ በአህያ ላይ የሚጭኑ ሰዎች አየሁ፤ ይህን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ያስገቡ የነበረው በሰንበት ቀን ነበረ። ስለዚህ በዚያን ቀን ምግብ እንዳይሸጡ ከለከልኋቸው። 16በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የጢሮስ ሰዎችም ዓሣና ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጥ በሰንበት ቀን እያመጡ ለይሁዳ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ይሸጡ ነበር። 17እኔም የይሁዳን መኳንንት በመገሠጽ እንዲህ አልኋቸው፤ “ሰንበትን በማርከስ ይህ የምትፈጽሙት ክፉ ድርጊት ምንድን ነው? 18የቀድሞ አባቶቻችሁ ያደረጉት ይህንኑ አልነበረምን? አምላካችንስ ይህን ሁሉ ጥፋት በእኛና በዚች ከተማ ላይ ያመጣው በዚሁ በደላችን አይደለምን? አሁንም እናንተ ሰንበትን በማርከስ የባሰ መከራ በእስራኤል ላይ ታመጣላችሁ።”
19በሰንበት ዋዜማ በኢየሩሳሌም በሮች ላይ የምሽቱ ጥላ ማረፍ ሲጀምር በሮቹ እንዲዘጉና፣ ሰንበት እስኪያልፍ ድረስ እንዳይከፈቱ አዘዝሁ፤ በሰንበት ቀን ጭነት እንዳይገባም ከራሴ ሰዎች አንዳንዶቹን በየበሩ ላይ አቆምሁ። 20የልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎችና ቸርቻሪዎች ከኢየሩሳሌም ውጭ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ዐድረዋል። 21እኔ ግን፣ “ከቅጥሩ ውጭ የምታድሩት ለምንድን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ዳግመኛ ብታደርጉ እጄን አነሣባችኋለሁ” ስል አስጠነቀቅኋቸው፤ እነርሱም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሰንበት ቀን አልመጡም። 22ከዚያም ሌዋውያኑ ራሳቸውን እንዲያነጹ፣ ሄደውም የቅጥሩን በር እንዲጠብቁና የሰንበትንም ቀን እንዲቀድሱ አዘዝኋቸው።
አምላኬ ሆይ፤ ስለዚህም ደግሞ አስበኝ፤ እንደ ታላቅ ፍቅርህም ብዛት ምሕረት አድርግልኝ።
23በእነዚያም ቀናት የአሽዶድን፣ የአሞንንና የሞዓብን ሴቶች ያገቡ አይሁድ አገኘሁ። 24ከልጆቻቸውም እኩሌቶቹ የአሽዶድን፣ ወይም ከሌሎቹ ሕዝቦች የአንዱን ቋንቋ እንጂ የአይሁድን ቋንቋ መናገር አይችሉም ነበር። 25እኔም ገሠጽኋቸው፤ ርግማንም አወረድሁባቸው። አንዳንዶቹን መታኋቸው፤ ጠጕራቸውንም ነጨሁ። በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ስል አማልኋቸው፤ “ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ። 26የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ኀጢአት የሠራው እንዲህ ከመሰለው ጋብቻ የተነሣ አይደለምን? በብዙ መንግሥታት መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም፤ በአምላኩም የተወደደ ነበረ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ አደረገው። ነገር ግን ባዕዳን ሴቶች ወደ ኀጢአት መሩት። 27እናንተም ደግሞ ባዕዳን ሴቶችን በማግባት ይህን የመሰለ ታላቅ በደል እንደምትፈጽሙና ለአምላካችንም ታማኞች እንዳልሆናችሁ መስማት ይገባናልን?”
28ከሊቀ ካህኑ ከኤልያሴብ ልጅ ከዮአዳ ልጆች አንዱ የሖሮናዊው የሰንባላጥ አማች ነበረ፤ እኔም ከአጠገቤ አባረርሁት።
29አምላኬ ሆይ፤ የክህነትን ማዕረግ፣ የክህነትንና የሌዋውያንን ቃል ኪዳን ስላረከሱ ዐስባቸው።
30ስለዚህ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ከማናቸውም ባዕድ ነገር ሁሉ አነጻኋቸው፤ የእያንዳንዱንም ተግባር በመለየት በየሥራ ቦታቸው መደብኋቸው። 31በተወሰነው ጊዜ ስለሚዋጣውም የማገዶ ዕንጨትና ስለ በኵራቱ መመሪያ ሰጠሁ።
አምላኬ ሆይ፤ በቸርነት አስበኝ።
Currently Selected:
ነህምያ 13: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.