በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ በሕዝቡ ጆሮ አነበቡ፥ አሞናውያንና ሞዓባውያንም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘላለም እንዳይገቡ የሚል በዚያ ተገኘ። የእስራኤልን ልጆች በእንጀራና በውኃ ስላልተቀበሉአቸውና ይረግማቸው ዘንድ በለዓምን ስለ ገዙባቸው ነው፥ ነገር ግን አምላካችን እርግማኑን ወደ በረከት መለሰው። ሕጉንም በሰሙ ጊዜ ድብልቁን ሕዝብ ሁሉ ከእስራኤል ለዩ። ከዚህም አስቀድሞ በአምላካችን ቤት ጓዳዎች ላይ ተሾሞ የነበረው ካህኑ ኤልያሴብ ከጦቢያ ጋር ተወዳጅቶ፥ ለሌዋውያን፥ ለመዘምራን፥ ለበረኞቹ እንደ ሕጉ የተሰጣቸውን የእህሉን ቁርባንና ዕጣኑን፥ ዕቃዎቹንም፥ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት፥ ለካህናቱም የሆነውን የማንሣት ቁርባን አስቀድሞ ያስቀመጡበትን ታላቁን ጓዳ አዘጋጅቶለት ነበር። እኔ ግን በባቢሎን ንጉሥ በአርጤክስስ በሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበርና በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም አልነበርሁም። ከጥቂት ዘመንም በኋላ የንጉሡን ፈቃድ ለመንሁ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣሁ፥ ኤልያሴብም በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦብያ ጓዳውን በማዘጋጀት ያደረገውን ክፉ ነገር አስተዋልሁ። እጅግም አስከፋኝ፥ የጦብያንም የቤቱን ዕቃ ሁሉ ከጓዳ ወደ ውጪ ጣልሁ። ጓዳዎቹንም እንዲያነጹ አዘዝሁ፥ የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃዎች የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም መልሼ በዚያ አገባሁ። ለሌዋውያንም እድል ፈንታቸው እንዳልተሰጠ፥ የሚያገለግሉትም ሌዋውያንና መዘምራን እያንዳንዱ ወደ እርሻው እንደ ሄዱ ተመለከትሁ። እኔም፦ የእግዚአብሔር ቤት ስለ ምን ተተወ? ብዬ ከአለቆቹ ጋር ተከራከርሁ። ሰበሰብኋቸውም፥ በየስፍራቸውም አቆምኋቸው። ይሁዳም ሁሉ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት ወደ ዕቃ ቤቶች አመጡ። በዕቃ ቤቶችም ላይ ካህኑን ሰሌምያን፥ ጸሐፊውንም ሳዶቅን፥ ከሌዋውያኑም ፈዳያን ሾምሁ፥ ከእነርሱም ጋር የመታንያ ልጅ የዘኩር ልጅ ሐናን ነበረ፥ እነርሱም የታመኑ ሆነው ተገኙ፥ ሥራቸውም ለወንድሞቻቸው ማከፋፈል ነበረ። አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ አስበኝ፥ ለአምላኬም ቤት ያደረግሁትን ወረታዬን አታጥፋ።
መጽሐፈ ነህምያ 13 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነህምያ 13:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች