መጽሐፈ ነህምያ 13:1-14

መጽሐፈ ነህምያ 13:1-14 አማ05

የኦሪት ሕግ ከፍ ባለ ድምፅ በተነበበላቸው ጊዜ ሰዎቹ ሲያዳምጡ “ሞአባውያንና ዐሞናውያን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ለዘለዓለም አይቀላቀሉ” ከሚለው አንቀጽ ደረሱ። ይህም ትእዛዝ የተሰጠበት ምክንያት እስራኤላውያን ከግብጽ ምድር በወጡበት ጊዜ በጒዞ ላይ ሳሉ ሞአባውያንና ዐሞናውያን ምግብና ውሃ ስለ ከለከሉአቸው ነበር፤ ይልቁንም ይህን በማድረግ ፈንታ ለበለዓም ገንዘብ ሰጥተው የእስራኤልን ሕዝብ እንዲረግምላቸው አድርገው ነበር፤ እግዚአብሔር ግን መርገሙን ወደ በረከት ለወጠው። ይህም ሕግ ሲነበብ እስራኤላውያን በሰሙት ጊዜ ባዕዳን የሆኑ ሕዝቦችን ከመካከላቸው አስወገዱ። የቤተ መቅደስ ዕቃ ግምጃ ቤት ኀላፊ የሆነው ካህኑ ኤልያሺብ ለረጅም ጊዜ ከጦቢያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው፤ ከዚህም የተነሣ የእህል መባ፥ ዕጣን፥ የቤተ መቅደስ ንዋያተ ቅድሳት፥ ከእህል፥ ከወይን ጠጅ፥ ከወይራ ዘይት ተውጣጥቶ ለሌዋውያኑ ለቤተ መቅደስ መዘምራንና ለዘብ ጠባቂዎች የሚሰጠው ዐሥራትና ለካህናቱ የሚሰጥ መባ ሁሉ እንዲቀመጥበት ታስቦ በተለይ የተሠራውን ታላቅ ክፍል ጦቢያ በመኖሪያነት ይጠቀምበት ዘንድ ኤልያሺብ ፈቅዶለት ነበር። ይህም ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ እኔ በኢየሩሳሌም አልነበርኩም፤ አርጤክስስ የባቢሎን ንጉሠ ነገሥት በሆነ በሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ወደ ባቢሎን ተመልሼ ሄጄ ነበር፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ከንጉሡ ፈቃድ ጠይቄ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለስኩ፤ እዚያም እንደ ደረስኩ ኤልያሺብ ለጦቢያ በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ አንድ መኖሪያ ክፍል የፈቀደለት መሆኑን ሰማሁ፤ በቊጣ ተነሥቼ የጦቢያን ንብረት ሁሉ ከክፍሉ በማስወጣት አሽቀንጥሬ ጣልኩ፤ ክፍሎቹም በሕጉ መሠረት በሥርዓት እንዲነጹና የቤተ መቅደሱም ንዋያተ ቅድሳት፥ የእህል መባውና ዕጣኑ ወደዚያ ተመልሰው እንዲገቡ ትእዛዝ ሰጠሁ። እንዲሁም አገልግሎቱን የሚፈጽሙት የቤተ መቅደሱ መዘምራንና ሌሎችም ሌዋውያን ኢየሩሳሌምን ለቀው በመውጣት ወደየእርሻቸው ተመልሰው መግባታቸውን ተገነዘብኩ፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ሕዝቡ ለመዘምራኑና ለሌዋውያኑ በቂ መተዳደሪያ ባለመስጠታቸው ነበር። ቤተ መቅደሱም ይህን ያኽል ቸል እስኪባል ዝም ብለው በመመልከታቸው ባለሥልጣኖችን ገሠጽኩ፤ ሌዋውያኑንና መዘምራኑንም ወደ ቤተ መቅደስ መልሼ በማምጣት ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አደረግሁ፤ ከዚህም በኋላ እስራኤላውያን ሁሉ እንደገና ከእህልና ከወይን ጠጅ፥ ከወይራ ዘይትም የሚፈለግባቸውን ከዐሥር አንድ እያወጡ ወደ ቤተ መቅደስ ዕቃ ግምጃ ቤት ማምጣት ጀመሩ። ለዕቃ ግምጃ ቤቱም ኀላፊነት ካህኑን ሼሌምያን፥ የሕግ ምሁሩን ሳዶቅንና ሌዋዊውን ፐዳያን መደብሁ፤ የማታንያ የልጅ ልጅ የሆነው የዛኩር ልጅ ሐናንም የእነርሱ ረዳት ነበር፤ እነዚህም ሰዎች ለሥራ ጓደኞቻቸው የሚሆነውን መተዳደሪያ ለማከፋፈል ታማኞች ነበሩ። አምላኬ ሆይ፥ ለቤተ መቅደስህና ለአገልግሎቱ መቃናት ስል እነዚህን ሁሉ በታማኝነት ማድረጌን በማሰብ ቸርነት አድርግልኝ።