ዘሌዋውያን 14

14
ከተላላፊ የቈዳ በሽታ የመንጻት ሥርዐት
1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ለምጻሙ ሰው እንዲነጻ ወደ ካህኑ በሚወስዱት ጊዜ ሥርዐቱ እንዲህ ነው፦ 3ካህኑ ከሰፈር ወደ ውጭ ወጥቶ ይመርምረው፤ ሰውየው ከተላላፊ የቈዳ በሽታው#14፥3 በትውፊት ለምጽ ይባላል። የዕብራይስጡ ቃል ከቈዳ ጋራ ለተያያዘ በሽታ አንድ ቃል ነው፤ በዚህ ምዕራፍ በሌላ ስፍራም ይገኛል። ተፈውሶ ከሆነ፣ 4ካህኑ ስለሚነጻው ሰው፣ ለመብላት ከተፈቀደው የወፍ ዐይነት ሁለት ከነሕይወታቸው፣ የዝግባ ዕንጨት፣ ደመቅ ያለ ቀይ ድርና ሂሶጵ እንዲያመጣ ይዘዝ። 5ካህኑም ከወፎቹ አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ባለ የምንጭ ውሃ ላይ እንዲታረድ ይዘዝ። 6በሕይወት ያለውንም ወፍ ከዝግባው ዕንጨት፣ ደመቅ ካለው ቀይ ድርና ከሂሶጵ ጋራ በምንጩ ውሃ ላይ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይንከር። 7ከተላላፊ በሽታ የሚነጻውንም ሰው ሰባት ጊዜ ይርጨው፤ መንጻቱንም ያስታውቅ፤ በሕይወት ያለውንም ወፍ ወደ ውጭ ይልቀቀው።
8“የሚነጻው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ጠጕሩን በሙሉ ይላጭ፤ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ በሥርዐቱም መሠረት ንጹሕ ይሆናል። ከዚህም በኋላ ወደ ሰፈር መግባት ይችላል፤ ነገር ግን ሰባት ቀን ከድንኳኑ ውጭ ይቈይ። 9በሰባተኛውም ቀን ጠጕሩን በሙሉ ይላጭ፤ ራሱን፣ ጢሙን፣ ቅንድቡንና ሌላውንም ጠጕር ሁሉ ይላጭ። ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።
10“በስምንተኛው ቀን እንከን የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ነውር የሌለባትን አንዲት የአንድ ዓመት እንስት በግ ያቅርብ፤ እንዲሁም ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ#14፥10 5 ኪሎ ግራም ይሆናል። የላመ ዱቄት ያቅርብ፤ ደግሞ አንድ ሎግ#14፥10 0.3 ሊትር ገደማ ይሆናል፤ እንዲሁም 12፣ 15፣ 21 እና 24 ይመ ዘይት ያምጣ። 11ሰውየው የነጻ መሆኑን የሚያስታውቀው ካህን የሚነጻውን ሰውና መሥዋዕቶቹን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ።
12“ካህኑም ከተባዕቱ ጠቦቶች በመውሰድ ከሎግ ዘይቱ ጋራ የበደል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ፤ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግም በእግዚአብሔር ፊት ይወዝውዛቸው። 13ጠቦቱንም፣ የኀጢአት መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት በተቀደሰው ስፍራ ይረደው፤ የኀጢአት መሥዋዕቱ ለካህኑ እንደሚሰጥ ሁሉ የበደል መሥዋዕቱም ለካህኑ ይሰጥ፤ ይህም እጅግ የተቀደሰ ነው። 14ካህኑ ከበደል መሥዋዕቱ ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ታችኛውን ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ። 15ካህኑም ከሎግ ዘይት ወስዶ በራሱ ግራ እጅ መዳፍ ውስጥ ይጨምር፤ 16ካህኑም የቀኝ እጁንም ጣት በመዳፉ በያዘው ዘይት ውስጥ በመንከር በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይርጭ። 17ካህኑ በመዳፉ ውስጥ ከቀረው ዘይት ጥቂቱን ወስዶ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ታችኛውን ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት በበደል መሥዋዕቱ ደም ላይ ደርቦ ይቅባ። 18ካህኑም በመዳፉ ላይ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያድርግ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ያስተስርይለት።
19“ካህኑም የኀጢአት መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ከርኩሰቱ ለሚነጻውም ሰው ያስተስርይለት፤ ከዚህ በኋላ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ይረድ፤ 20ካህኑም ከእህል ቍርባኑ ጋራ በመሠዊያው ላይ በማቅረብ ያስተስርይለት፤ ሰውየውም ንጹሕ ይሆናል።
21“ሰውየው ድኻ ከሆነና እነዚህን ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደለት፣ ማስተስረያ እንዲሆነው የሚወዘወዝ አንድ ተባዕት የበግ ጠቦት ለበደል መሥዋዕት፣ በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ#14፥21 2 1.6 ኪሎ ግራም ይሆናል። የላመ ዱቄት ለእህል ቍርባን ያቅርብ፤ ደግሞም አንድ ሎግ ዘይት ያምጣ፤ 22እንዲሁም ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ዐቅሙ የፈቀደውን አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ።
23“እነዚህንም በስምንተኛው ቀን ስለ መንጻቱ ሥርዐት ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። 24ካህኑም ለበደል መሥዋዕት የሚሆነውን የበግ ጠቦትና አንድ ሎግ ዘይት ይቀበል፤ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግም በእግዚአብሔር ፊት ይወዝውዛቸው። 25ለበደል መሥዋዕት የሚሆነውንም የበግ ጠቦት ይረድ፤ ካህኑም ከደሙ ጥቂት ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮ ታችኛ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ፤ 26ካህኑም ከዘይቱ ጥቂቱን በግራ እጁ መዳፍ ውስጥ ያፍስስ፤ 27ካህኑም የቀኝ እጁን ጣት በመዳፉ በያዘው ዘይት ውስጥ በመንከር በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጭ። 28ካህኑም በመዳፉ ከያዘው ዘይት ጥቂቱን ወስዶ የበደል መሥዋዕቱን ደም ባስነካበት ቦታ፣ ይኸውም የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ። 29ካህኑ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለት ዘንድ በመዳፉ ከያዘው ዘይት የቀረውን በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያፍስስ፤ 30ካህኑም ርግቦቹን ወይም የዋኖሶቹን ጫጩቶች የሰውየው ዐቅም የፈቀደውን ይሠዋል፤ 31ከእነዚህም አንዱን#14፥31 የሰብዓ ሊቃናትና የሱርሰት ትርጕሞች ከዚህ ጋራ ይስማማሉ፤ ዕብራይስጡ 31 የሰውየው ዐቅም የፈቀደውን ያህል አንዱን ለኀጢአት ይላል ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ከእህሉ ቍርባን ጋራ ያቅርብ፤ በዚህም ሁኔታ ካህኑ ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል።”
32ተላላፊ የቈዳ በሽታ ይዞት የሚነጻበትን መደበኛ መሥዋዕት ለማቅረብ ዐቅም ላነሰው ሰው ሕጉ ይህ ነው።
ልብስ ላይ ከሚታይ ተላላፊ በሽታ መንጻት
33 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 34“ርስት አድርጌ ወደምሰጣቸው ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፣ በዚያ አገር አንዱን ቤት በተላላፊ በሽታ የበከልሁ እንደ ሆነ፣ 35ባለቤቱ ወደ ካህኑ ሄዶ፣ ‘በቤቴ ውስጥ ተላላፊ በሽታ የሚመስል ነገር አይቻለሁ’ ብሎ ይንገረው። 36ካህኑ ወደዚያ ቤት በመግባት በሽታውን መርምሮ ርኩስ መሆኑን ከማስታወቁ በፊት፣ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ይዘዝ፤ ከዚህ በኋላ ካህኑ ወደ ቤቱ ገብቶ ይመርምር። 37በግድግዳው ላይ ያለውን ተላላፊ በሽታ በሚመረምርበት ጊዜ፣ መልኩ ወደ አረንጓዴነት ወይም ወደ ቀይነት የሚያደላ የተቦረቦረ ነገር በግድግዳው ቢታይ፣ 38ካህኑ ከቤቱ ወደ ደጅ ወጥቶ ቤቱን ሰባት ቀን ይዝጋው። 39ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቤቱን ለመመርመር ይመለስ፤ ተላላፊው በሽታ በግድግዳው ተስፋፍቶ ቢገኝ፣ 40ካህኑ የተበከሉት ድንጋዮች ተሰርስረው እንዲወጡና ከከተማው ውጭ ባለው ርኩስ ስፍራ እንዲጣሉ ይዘዝ፤ 41የቤቱ ግድግዳ በሙሉ በውስጥ በኩል እንዲፋቅና ፍቅፋቂው ከከተማው ውጭ ባለው ርኩስ ስፍራ እንዲደፋ ያድርግ። 42በወጡትም ድንጋዮች ቦታ ሌሎች ድንጋዮች አምጥተው ይተኩ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይምረጉ።
43“ድንጋዮቹ ወጥተው፣ ቤቱ ከተፈቀፈቀና ከተመረገ በኋላ ተላላፊው በሽታ እንደ ገና በቤቱ ውስጥ ከታየ፣ 44ካህኑ ሄዶ ይመርምረው፤ ተላላፊው በሽታ በቤቱ ውስጥ ተስፋፍቶ ከተገኘ፣ አደገኛ በሽታ ነው፤ ቤቱም ርኩስ ነው። 45ስለዚህ ቤቱ ይፍረስ፤ ድንጋዩ፣ ዕንጨቱና ምርጊቱ በሙሉ ከከተማ ውጭ ባለው ርኩስ ስፍራ ይጣል።
46“ቤቱ ተዘግቶ ሳለ ማንኛውም ሰው ቢገባበት፣ ያ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 47በዚያ ቤት ገብቶ የተኛ ወይም የበላ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ይጠብ።
48“ነገር ግን ቤቱ ከተመረገ በኋላ፣ ካህኑ ሊመረምረው በሚመጣበት ጊዜ ተላላፊው በሽታ ሳይስፋፋ ቢገኝ፣ በሽታው ስለ ለቀቀው ቤቱ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ። 49ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፣ የዝግባ ዕንጨት፣ ደመቅ ያለ ቀይ ድርና ሂሶጵ ያቅርብ። 50ከወፎቹም አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ባለ የምንጭ ውሃ ላይ ይረድ። 51የዝግባውን ዕንጨት፣ ሂሶጱን፣ ደመቅ ያለውን ቀይ ድርና በሕይወት ያለውን ወፍ ወስዶ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውሃ ውስጥ ይንከር፤ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይርጭ። 52ቤቱንም በወፉ ደም፣ በምንጩ ውሃ፣ በሕይወት ባለው ወፍ፣ በዝግባው ዕንጨት፣ በሂሶጱና ደመቅ ባለው ቀይ ድር ያንጻው። 53በሕይወት ያለውንም ወፍ ከከተማ ወደ ውጭ ይልቀቀው፤ በዚህ ሁኔታ ለቤቱ ያስተሰርይለታል፤ ቤቱም ንጹሕ ይሆናል።”
54ይህ ሕግ ለማንኛውም ተላላፊ የቈዳ በሽታ፣ ለሚያሳክክ ሕመም፣ 55በልብስና በቤት ላይ ለሚመጣ ተላላፊ በሽታ፣ 56ለዕብጠት፣ ለችፍታ ወይም ለቋቍቻ፣ 57አንድ ነገር ንጹሕ ወይም ርኩስ መሆኑ የሚታወቅበት ነው። ይህ ለተላላፊ የቈዳ በሽታ እንዲሁም በልብስና በቤት ላይ ለሚወጣ ተላላፊ በሽታ የሚያገለግል ሕግ ነው።

Currently Selected:

ዘሌዋውያን 14: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ