ዘሌዋውያን 15
15
የሚያረክስ የሰውነት ፈሳሽ
1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብላችሁ ንገሯቸው፤ ‘ማንም ሰው ከሰውነቱ ፈሳሽ ነገር ቢወጣ ያ ሰው ርኩስ ነው። 3ከሰውነቱ የሚወጣው ፈሳሽ መፍሰሱን ቢቀጥል ወይም ባይቀጥል ሰውየው ርኩስ ነው፤ ፈሳሹም ርኩሰት የሚያስከትለው እንደዚህ ነው፦
4“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው የተኛበት የትኛውም መኝታ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ የተቀመጠበት ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል። 5ዐልጋውን የነካ ማንኛውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 6ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው በተቀመጠበት በየትኛውም ነገር ላይ የተቀመጠ ሰው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል።
7“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣውን ሰው የነካ ማንኛውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል።
8“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው ንጹሕ በሆነ ሰው ላይ ቢተፋ፣ የተተፋበት ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል።
9“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው የተቀመጠበት ኮርቻ ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ 10ከበታቹ ያለውንም ነገር ሁሉ የነካ ማንም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። እነዚህንም ነገሮች የሚያነሣ ማንም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል።
11“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው እጁን በውሃ ሳይታጠብ ሌላውን ሰው ቢነካ፣ የተነካው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል።
12“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው የነካው የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ ከዕንጨት የተሠራ ዕቃ ከሆነ በውሃ ይታጠብ።
13“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው ከፈሳሹ ሲነጻ፣ በሕጉ መሠረት ለመንጻቱ ሰባት ቀን ይቍጠር፤ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በምንጭ ውሃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። 14በስምንተኛውም ቀን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ይዞ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በመቅረብ ለካህኑ ይስጥ። 15ካህኑም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ በዚህ መሠረት ስለ ፈሳሹ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለሰውየው ያስተሰርይለታል።
16“ ‘አንድ ሰው ዘሩ በሚፈስስበት ጊዜ ሰውነቱን በሙሉ በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 17የፈሰሰው ዘር የነካው ማንኛውም ልብስ ወይም ቍርበት በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 18አንድ ሰው ከአንዲት ሴት ጋር ግብረ ሥጋ ፈጽሞ ዘር ቢፈስሰው፣ ሁለቱም በውሃ ይታጠቡ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩሳን ይሆናሉ።
19“ ‘ሴት ጊዜውን እየጠበቀ የሚመጣው የደም መፍሰስ ቢኖርባት፣ የወር አበባዋ ርኩሰት እስከ ሰባት ቀን ይቈያል፤ በዚህ ጊዜ ማንም ሰው ቢነካት እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
20“ ‘በወር አበባዋ ጊዜ የምትተኛበት ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል፤ የተቀመጠችበትም ነገር ርኩስ ይሆናል። 21መኝታዋን የነካ ማንኛውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 22የተቀመጠችበትን ማንኛውንም ነገር የነካ ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል፤ 23መኝታዋን ወይም የተቀመጠችበትን ማንኛውንም ነገር የነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
24“ ‘አንድ ሰው ከእርሷ ጋር ቢተኛና የወር አበባዋ ቢነካው፣ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ የሚተኛበት መኝታ ሁሉ ርኩስ ይሆናል።
25“ ‘ሴት ከወር አበባዋ ጊዜ ሌላ ብዙ ቀን ደም ቢፈስሳት፣ ወይም የወር አበባዋ ጊዜ ካለፈ በኋላ የደሙ መፍሰስ ባይቋረጥ፣ ልክ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ፣ ደም መፍሰሱ እስኪቆም ድረስ ርኩስ ትሆናለች። 26ደሟ መፍሰሱን በቀጠለበት ጊዜ ሁሉ፣ የምትተኛበት ማንኛውም መኝታ ልክ በወር አበባዋ ጊዜ እንደ ነበረው መኝታ ርኩስ ይሆናል፤ የምትቀመጥበትም ማንኛውም ነገር ልክ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ ርኩስ ይሆናል። 27እነዚህንም የሚነካ ማንኛውም ሰው ርኩስ ይሆናል፤ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል።
28“ ‘ከደሟ ፍሳሽ ሳትነጻ ሰባት ቀን ትቍጠር፤ ከዚያም በኋላ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ ትሆናለች። 29በስምንተኛውም ቀን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ይዛ በመቅረብ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለካህኑ ትሰጣለች። 30ካህኑም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ በዚህ መሠረት ስለ ፈሳሽዋ ርኩሰት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይላታል።
31“ ‘በመካከላቸው ያለችውን ማደሪያዬን#15፥31 ወይም የመገናኛ ድንኳኔን እንዳያረክሱና በርኩሰታቸው እንዳይሞቱ፣ እስራኤላውያንን ከሚያረክሳቸው ነገር ለዩአቸው።’ ”
32ፈሳሽ ነገር የሚወጣውን፣ ዘሩም በመፍሰሱ ርኩስ የሆነውን ሰው ሁሉ፣ 33በወር አበባ ላይ ያለችን ሴት፣ ፈሳሽ ነገር የሚወጣቸውን ወንድ ወይም ሴት፣ በሥርዐቱ መሠረት ርኩስ ከሆነች ሴት ጋር የሚተኛውን ወንድ በሚመለከት ሕጉ ይኸው ነው።
Currently Selected:
ዘሌዋውያን 15: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.