የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘሌዋውያን 13

13
ተላላፊ የቈዳ በሽታ
1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2“ማንኛውም ሰው በሰውነቱ ቈዳ ላይ ዕብጠት ወይም ችፍታ ወይም ቋቍቻ ቢወጣበትና ይህም ወደ ተላላፊ የቈዳ በሽታ#13፥2 በልማድ ለምጽ ይባላል፤ የዕብራይስጡ ቃል ከቈዳ ጋር ለተያያዘ በሽታ ሁሉ የሚገባ ነው። በዚህ ምዕራፍ ሌላም ስፍራ ይገኛል። የሚለወጥበት ከሆነ፣ ወደ ካህኑ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ልጆቹ#13፥2 ወይም ዘሮቹ ወደ አንዱ ያምጡት። 3ካህኑም በሰውየው ቈዳ ላይ ያለውን ቍስል ይመርምር፤ በቍስሉ በተበከለው አካባቢ ያለው ጠጕር ወደ ነጭነት ተለውጦ ቢያገኘውና ቦታው ጐድጕዶ#13፥3 ወይም ከሌላው የቈዳ ክፍል ጠልቆ ቢገባ፤ በዚህ ምዕራፍ በሌላ ስፍራም ይገኛል። ወደ ውስጥ ቢገባ፣ ይህ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። ካህኑም መርምሮ ይህን ባወቀ ጊዜ፣ ሰውየው በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ርኩስ መሆኑ ይገለጽ። 4በቈዳው ላይ ያለው ቋቁቻ ነጭ ሆኖ ቢታይ፣ ነገር ግን ከቈዳው በታች ዘልቆ ባይገባና በቦታው ላይ የሚገኘው ጠጕር ወደ ነጭነት ባይለወጥ፣ ካህኑ በሽተኛውን ሰባት ቀን ያግልለው። 5በሰባተኛውም ቀን ካህኑ በሽተኛውን ይመርምረው፤ ቍስሉ ለውጥ ካላመጣና በቈዳውም ላይ ካልተስፋፋ እንደ ገና ሰባት ቀን ያግልለው። 6በሰባተኛው ቀን ካህኑ እንደ ገና ይመርምረው፤ ቍስሉ ከከሰመና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ቍስሉ ችፍታ እንጂ ሌላ አይደለም። ሰውየው ልብሱን ይጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። 7ራሱን ለካህን አሳይቶ መንጻቱ ከታወቀ በኋላ፣ ችፍታው በቈዳው ላይ እየተስፋፋ ከሆነ፣ እንደ ገና ካህኑ ፊት ይቅረብ፤ 8ካህኑም ይመርምረው፤ ችፍታው በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ከተገኘ፣ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው።
9“ማንኛውም ሰው ተላላፊ የቈዳ በሽታ ከያዘው፣ ወደ ካህኑ ያምጡት፤ 10ካህኑም ይመርምረው፤ በሰውነቱ ላይ ጠጕሩን ወደ ነጭነት የለወጠ ነጭ ዕባጭ ካለና በዕብጠቱም ውስጥ ቀይ ሥጋ ቢታይ፣ 11ሥር የሰደደ የቈዳ በሽታ ነውና ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ርኩስ መሆኑ ግልጽ ስለሆነም ሰውየውን አያግልለው።
12“ደዌው በአካላቱ ሁሉ ላይ በመውጣት በሽተኛውን ከራስ ጠጕር እስከ እግር ጥፍር ያለበሰው መሆኑን ካህኑ እስካየ ድረስ፣ 13ካህኑ ይመርምረው፤ ደዌው የሰውየውን ሰውነት ሙሉ በሙሉ ሸፍኖት ከተገኘ፣ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ሙሉ በሙሉ ነጭ ስለሆነ ንጹሕ ነው፤ 14ነገር ግን ቍስሉ አመርቅዞ ቀይ ሥጋ ቢታይበት ርኩስ ይሁን። 15ካህኑም የተገለጠውን ቀይ ሥጋ በሚያይበት ጊዜ ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ፤ ቀይ ሥጋ ርኩስ ስለሆነ፣ ተላላፊ በሽታ ነው። 16ቀይ ሥጋ ተለውጦ ከነጣ ግን ወደ ካህኑ ይሂድ፤ 17ካህኑም ይመርምረው፤ ቍስሎች ወደ ነጭነት ተለውጠው ከተገኙ፣ የታመመው ሰው ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ንጹሕም ይሆናል።
18“አንድ ሰው በገላው ላይ ዕባጭ ወጥቶ ቢድን፣ 19ዕባጩ በነበረበት ቦታ ላይም ነጭ ዕብጠት ወይም ነጣ ያለ ቀይ ቋቍቻ ቢታይ፣ ካህኑ ዘንድ ይቅረብ። 20ካህኑም ይመርምረው፤ ከቈዳው በታች ዘልቆ የገባ ቢሆን በቦታውም ያለው ጠጕር ቢነጣ፣ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። 21ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ነጭ ጠጕር በውስጡ ከሌለ፣ ዘልቆ ካልገባና የከሰመ ቢሆን፣ ካህኑ ሰባት ቀን ያግልለው። 22በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ካገኘውም፣ ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ የሚተላለፍ ነው። 23ቋቍቻው ግን ባለበት ከቈየና ወደ ሌላ ስፍራ ካልተስፋፋ፣ የዕባጩ ጠባሳ እንጂ ሌላ አይደለም፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ።
24“አንድ ሰው እሳት ቈዳውን ቢያቃጥለውና በተቃጠለው ስፍራ ነጣ ያለ ቀይ ወይም ነጭ ቋቍቻ ቢታይበት፣ 25ካህኑ ይመርምረው፤ ቋቍቻው ባለበትም ቦታ ያለው ጠጕር ቢነጣና ከቈዳው በታች ዘልቆ ቢገባ፣ በቃጠሎው ሰበብ ከውስጥ የወጣ ተላላፊ በሽታ ነው፤ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። 26ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ነጭ ጠጕር የሌለበት፣ ከቈዳውም በታች ዘልቆ ያልገባና የከሰመ ቢሆን፣ ካህኑ ሰውየውን ሰባት ቀን ያግልለው። 27በሰባተኛው ቀን ካህኑ ይመርምረው፤ በሽታውም በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ቢያገኘው፣ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። 28ቋቍቻ ባለበት ከቈየና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ይልቁንም እየከሰመ ከሄደ፣ በቃጠሎው ሰበብ የተከሠተ ዕብጠት ነውና ካህኑ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ የቃጠሎው ጠባሳ እንጂ ሌላ አይደለም።
29“በወንድ ወይም በሴት ዐናት ወይም አገጭ ላይ ቍስል ቢወጣ፣ 30ካህኑ ቍስሉን ይመርምር፤ ከቈዳው በታች ዘልቆ ከገባ፣ በውስጡም ያለው ጠጕር ቢጫና ቀጭን ከሆነ ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ የሚያሳክክ የራስ ወይም የአገጭ ተላላፊ በሽታ ነው። 31ካህኑ እንዲህ ዐይነቱን ቍስል በሚመረምርበት ጊዜ፣ ከቈዳው በታች ዘልቆ ካልገባና በውስጡም ጥቍር ጠጕር ከሌለ፣ ካህኑ ሰውየውን ሰባት ቀን ያግልለው። 32ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቍስሉን ይመርምር፤ የሚያሳክከው ቦታ ያልሰፋ፣ ቢጫ ጠጕር የሌለውና ከቈዳው በታች ዘልቆ ያልገባ ከሆነ፣ 33ከቈሰለው ቦታ በስተቀር ጠጕሩን ይላጭ፤ ካህኑ ሰባት ተጨማሪ ቀን ሰውየውን ያግልል። 34ካህኑ በሰባተኛው ቀን የሚያሳክከውን የሰውየውን ቍስል ይመርምር፤ በቈዳው ላይ ካልሰፋና ከቈዳው በታች ዘልቆ ካልገባ ካህኑ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ልብሱን ዐጥቦ ንጹሕ ይሁን። 35ንጹሕ መሆኑ ከተገለጠ በኋላ ግን የሚያሳክከው ቍስል ተስፋፍቶ ቢገኝ፣ 36ካህኑ ይመርምረው፤ ቍስሉ በቈዳው ላይ ከሰፋ፣ ካህኑ የጠጕሩን ቢጫ መሆን አለመሆን ማየት አያሻውም፤ ሰውየው ርኩስ ነው። 37ነገር ግን ቍስሉ በካህኑ አመለካከት ለውጥ ያላሳየ ከሆነና በውስጡ ጥቍር ጠጕር ካበቀለ ቍስሉ ድኗል፤ ሰውየው ነጽቷል፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ።
38“በወንድ ወይም በሴት ቈዳ ላይ ቋቍቻ ቢወጣ፣ 39ካህኑ ይመርምራቸው፤ ቋቍቻው ዳለቻ ከሆነ፣ በቈዳ ላይ የወጣ ጕዳት የማያስከትል ችፍታ ነው፤ ሰውየውም ንጹሕ ነው።
40“አንድ ሰው የራሱ ጠጕር ከዐናቱ ዐልቆ መላጣ ቢሆን ንጹሕ ነው። 41ጠጕሩ ከፊት ለፊት ተመልጦ ራሰ በራ ቢሆንም ንጹሕ ነው። 42ነገር ግን በመላጣው ወይም በበራው ላይ ነጣ ያለ ቀይ ቍስል ቢወጣበት፣ ያ ከመላጣው ወይም ከበራው የወጣ ተላላፊ በሽታ ነው። 43ካህኑ ይመርምረው፤ በመላጣው ወይም በበራው ላይ ያበጠው ተላላፊ የቈዳ በሽታ የሚመስል ነጣ ያለ ቍስል ከሆነ፣ 44ሰውየው ደዌ አለበት፤ ርኩስም ነው፤ በራሱ ላይ ካለው ቍስል የተነሣም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ።
45“እንዲህ ያለ ተላላፊ በሽታ ያለበት ሰው የተቀደደ ልብስ ይልበስ፤ ጠጕሩን ይግለጥ፤#13፥45 ወይም ራሱንም አይሸፍን እስከ አፍንጫውም ድረስ ተሸፋፍኖ ‘ርኩስ ነኝ! ርኩስ ነኝ!’ እያለ ይጩኽ። 46ተላላፊ በሽታው እስካለበት ጊዜ ድረስ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጥ፤ ከሰፈር ውጪም ይኑር።
በልብስ ላይ የሚታይ ተላላፊ በሽታ
47“ከበግ ጠጕር ወይም ከበፍታ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት ልብስ በተላላፊ በሽታ ቢበከል፣ 48በሸማኔ ዕቃ ወይም በእጅ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት የበግ ጠጕር ወይም የበፍታ ልብስ ወይም ማንኛውም ቈዳ ወይም ከቈዳ የተሠራ ነገር ቢሆን፣ 49በልብስ ወይም በዐጐዛ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራ ወይም በእጅ በተጠለፈ ወይም ከቈዳ በተሠራ ዕቃ ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ መሳይ ደዌ ቢከሠት፣ እየሰፋ የሚሄድ ተላላፊ በሽታ ስለሆነ ካህኑ ይየው። 50ካህኑ ደዌውን ይመርምር፤ በደዌ የተበከለውንም ዕቃ ሰባት ቀን ያግልል። 51በሰባተኛውም ቀን ይመርምረው፤ ደዌው በልብሱ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ወይም ለማናቸውም አገልግሎት በሚውል ዐጐዛ ላይ ተስፋፍቶ ቢገኝ፣ ክፉ ደዌ ነው፤ ዕቃውም ርኩስ ነው። 52ልብሱን ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራውን ወይም በእጅ የተጠለፈውን የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ወይም ደዌው ያለበትን ማንኛውንም ከቈዳ የተሠራ ዕቃ ያቃጥል፤ ደዌው ክፉ ነውና፤ ዕቃው ይቃጠል።
53“ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ደዌው በልብሱ ወይም በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ላይ፣ ወይም ከቈዳ በተሠራው ዕቃ ላይ ተስፋፍቶ ካልተገኘ፣ 54ካህኑ ደዌው ያለበት ነገር እንዲታጠብ ይዘዝ፤ ዕቃውንም ሰባት ቀን ደግሞ ያግልል። 55ደዌው ያለበት ዕቃ ከታጠበ በኋላ ካህኑ ይመርምረው፤ ደዌው ባይስፋፋም እንኳ መልኩን ካልለወጠ፣ ርኩስ ነው፤ ደዌው የወጣው በውስጥም ሆነ በውጭ ዕቃው በእሳት ይቃጠል። 56ዕቃው ከታጠበ በኋላ ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ደዌው ከስሞ ቢገኝ፣ በደዌ የተበከለውን ቦታ ከልብሱ ወይም ከቈዳው ወይም በሸማኔ ዕቃ ከተሠራው ወይም በእጅ ከተጠለፈው ጨርቅ ቀዶ ያውጣ። 57ነገር ግን ደዌው በልብሱ ወይም በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ላይ ወይም ከቈዳ በተሠራው ዕቃ ላይ ቢታይ፣ መስፋፋቱ ስለሆነ ደዌው ያለበት ማንኛውም ነገር በእሳት ይቃጠል። 58ታጥቦ ከደዌ የጠራ ልብስ ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራ ወይም በእጅ የተጠለፈ ጨርቅ ወይም ከቈዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ እንደ ገና ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።”
59ከበግ ጠጕር ወይም ከበፍታ የተሠራ ልብስ ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራ ወይም በእጅ የተጠለፈ ጨርቅ ወይም ከቈዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ በደዌ ቢበከል፣ ንጹሕ ወይም ርኩስ መሆኑን ለማወቅ ሕጉ ይህ ነው።

Currently Selected:

ዘሌዋውያን 13: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ