ኤርምያስ 10:1-13

ኤርምያስ 10:1-13 NASV

የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እግዚአብሔር የሚላችሁን ስሙ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የአሕዛብን መንገድ አትከተሉ፤ እነርሱ በሰማይ ምልክቶች ይታወካሉ፣ እናንተ ግን በእነዚህ አትረበሹ። የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ ዛፍ ከጫካ ይቈርጣሉ፤ የእጅ ጥበብ ባለሙያ በመሣሪያው ቅርጽ ያበጅለታል። በብርና በወርቅ ይለብጡታል፤ እንዳይወድቅም፣ በመዶሻ መትተው በምስማር ያጣብቁታል። ጣዖቶቻቸው በኪያር ዕርሻ መካከል እንደ ቆመ ማስፈራርቾ ናቸው፤ የመናገር ችሎታ የላቸውም፤ መራመድም ስለማይችሉ፣ ተሸካሚ ያስፈልጋቸዋል፤ ጕዳት ማድረስም ሆነ፣ መልካምን ነገር ማድረግ ስለማይችሉ፣ አትፍሯቸው።” እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ አንተ ታላቅ ነህ፤ የስምህም ሥልጣን ታላቅ ነው። የሕዝቦች ሁሉ ንጉሥ ሆይ፤ አንተን የማይፈራ ማነው? ክብር ይገባሃልና። ከምድር ጠቢባን ሁሉ፣ ከመንግሥቶቻቸውም ሁሉ መካከል፣ እንደ አንተ ያለ የለም። ከከንቱ የዕንጨት ጣዖት ትምህርት የሚቀሥሙ ሁሉ፣ ጅሎችና ሞኞች ናቸው። የተጠፈጠፈ ብር ከተርሴስ፣ ወርቅም ከአፌዝ ይመጣል። የእጅ ጥበብ ባለሙያና አንጥረኛው የሠሯቸው፣ ብልኀተኞችም ያበጇቸው ሁሉ፣ ሰማያዊና ሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፈዋል። እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱ ሕያው አምላክ፣ ዘላለማዊም ንጉሥ ነው፤ በሚቈጣበት ጊዜ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ መንግሥታትም ቍጣውን ሊቋቋሙ አይችሉም። “እናንተም፣ ‘እነዚህ ሰማያትንና ምድርን ያልፈጠሩ አማልክት ከምድር ላይ፣ ከሰማያትም በታች ይጠፋሉ’ ትሏቸዋላችሁ።” እርሱ ግን ምድርን በኀይሉ ፈጠረ፤ ዓለምን በጥበቡ መሠረተ፤ ሰማያትንም በማስተዋሉ ዘረጋ። ድምፁን ባንጐደጐደ ጊዜ በሰማይ ውሆች ይናወጣሉ፤ ጉሙን ከምድር ዳርቻ ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፤ መብረቅን ከዝናብ ጋራ ይልካል፤ ነፋስንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።