አስቴር 9:1-10

አስቴር 9:1-10 NASV

አዳር በተባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር ዐሥራ ሦስተኛ ቀን፣ በንጉሡ ትእዛዝ የወጣው ዐዋጅ የሚፈጸምበት ዕለት ነበር። በዚህም ዕለት የአይሁድ ጠላቶች የበላይነቱን እንደሚያገኙ ተማምነው ነበር፤ ሁኔታው ግን ተለወጠና አይሁድ በሚጠሏቸው ላይ የበላይነትን አገኙ። የእነርሱን መጥፋት በሚፈልጉ ወገኖች ላይ አደጋ ለመጣል አይሁድ በንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃዎች ሁሉ ባሉት ከተሞቻቸው ተሰበሰቡ። የሌሎቹ አገር ዜጎች ሕዝብ ሁሉ ፈርተዋቸው ስለ ነበር፣ ማንም ሊደፍራቸው አልቻለም። የየአውራጃው መኳንንት ሁሉ፣ እንደራሴዎች፣ የአውራጃ ገዦች እንዲሁም የንጉሡ አስተዳዳሪዎች አይሁድን ረዷቸው፤ ይህን ያደረጉትም መርዶክዮስን ስለ ፈሩ ነበር። መርዶክዮስ በቤተ መንግሥቱ ታዋቂ ሆነ፤ ዝናው በየአውራጃው ሁሉ ተሰማ፤ ኀይሉም እየበረታ ሄደ። ስለዚህ አይሁድ ጠላቶቻቸውን ሁሉ በሰይፍ እየመቱ ገደሏቸው፤ አጠፏቸውም፤ በሚጠሏቸውም ላይ ደስ ያላቸውን አደረጉ። አይሁድ በሱሳ ግንብ ዐምስት መቶ ሰው ገደሉ፤ አጠፉም። ፖርሻንዳታን፣ ደልፎንን፣ አስፓታን፣ ፖራታን፣ አዳልያን፣ አሪዳታን፣ ፓርማ ሽታን፣ አሪሳይን፣ አሪዳይንና ዋይዛታንም ገደሉ፤ እነዚህም የአይሁድ ጠላት የሆነው የሐመዳቱ ልጅ የሐማ ዐሥር ወንዶች ልጆች ነበሩ። በምርኮው ላይ ግን እጃቸውን አልዘረጉም።