መጽሐፈ አስቴር 9:1-10

መጽሐፈ አስቴር 9:1-10 አማ05

አዳር ተብሎ የሚጠራው ወር ዐሥራ ሦስተኛ ቀን እነሆ ደረሰ፤ ያም ዕለት የአይሁድ ጠላቶች ሁሉ አይሁድን በቊጥጥራቸው ሥር ስለ ማድረግ የወጣውን ንጉሣዊ ዐዋጅ ለመፈጸም የተዘጋጁበት ቀን ነበር፤ ነገር ግን ሁኔታው ተለውጦ አይሁድ በእነርሱ ላይ ድልን ተቀዳጁ። በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት በየከተማው አይሁድ በመኖሪያ ሰፈራቸው ሁሉ ጒዳት ሊያደርስባቸው በሚፈልግ በማንኛውም ሰው ላይ አደጋ ለመጣል በሚያስችላቸው ሁኔታ ተደራጁ፤ በየትኛውም ስፍራ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ስለ ፈሩአቸው ማንም እነርሱን ለመቋቋም አልደፈረም። እንዲያውም የየሀገሩ ገዢዎችና አስተዳዳሪዎች ሌሎችም ባለሥልጣኖችና የመንግሥት ተወካዮች ሁሉ አይሁድን ረዱአቸው፤ ይህንንም ያደረጉት መርዶክዮስን በመፍራት ነበር። መርዶክዮስ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግዛት ውስጥ በቤተ መንግሥት ከፍተኛ ሥልጣን የተሰጠው ታላቅ ሰው መሆኑና ኀይሉም እየበረታ መሄዱ በደንብ ታወቀ። በዚህ ዐይነት አይሁድ በጠላቶቻቸው ላይ የፈለጉትን ለማድረግ ቻሉ፤ በሰይፍ እያጠቁም ጨፈጨፉአቸው። አይሁድ መናገሻ ከተማ በሆነችው በሱሳ ብቻ እንኳ አምስት መቶ ሰው ፈጁ። ከነዚህም ውስጥ ፓርሻንዳታ፥ ዳልፎን፥ አስፓታ፥ ፖራታ፥ አዳልያ፥ አሪዳታ፥ ፓርማሽታ፥ አሪሳይ፥ አሪዳይና ዋይዛታ ተብለው የሚጠሩት የሃመዳታ ልጅ የሆነው የአይሁድ ጠላት የሃማን ልጆች ይገኙባቸዋል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን የንብረት ዝርፊያ አላካሄዱም።