ጳውሎስና ሲላስም በአንፊጶልና በአጶሎንያ ዐልፈው ወደ ተሰሎንቄ ሄዱ፤ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበር። ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሦስት ሰንበትም ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነርሱ ጋር ተነጋገረ፤ ክርስቶስ መከራን መቀበል እንዳለበትና ከሙታንም መነሣት እንደሚገባው እያስረዳ በማረጋገጥ፣ “ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው” አላቸው። አይሁድም አንዳንዶቹ የሰሙትን በመቀበል ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤ ደግሞም ቍጥራቸው ብዙ የሆነ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ግሪኮችና አያሌ ዕውቅ ሴቶች የሰሙትን ተቀብለው ከእነርሱ ጋር ተባበሩ። አይሁድ ግን ስለ ቀኑ ወስላቶችን ከገበያ ቦታ አሰባሰቡ፤ ሕዝቡንም አነሣሥተው በከተማው ውስጥ ሁከት ፈጠሩ፤ ጳውሎስንና ሲላስንም አምጥተው ሕዝቡ ፊት ለማቅረብ ወደ ኢያሶን ቤት እየተጣደፉ ሄዱ፤ ነገር ግን ሊያገኟቸው አልቻሉም፤ ስለዚህ ኢያሶንንና ሌሎች ወንድሞችን በከተማው ባለ ሥልጣናት ፊት እየጐተቷቸው እንዲህ እያሉ ጮኹ፤ “እነዚህ ሰዎች ዓለሙን ሁሉ ሲያውኩ ቈይተው፣ አሁን ደግሞ ወደዚህ መጥተዋል፤ ኢያሶንም በቤቱ ተቀብሏቸዋል፤ እነዚህም ሁሉ፣ ‘ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ’ በማለት የቄሳርን ሕግ የሚጥሱ ናቸው።” ሕዝቡና የከተማውም ሹማምት ይህን በሰሙ ጊዜ ተሸበሩ፤ ከዚያም ኢያሶንንና ሌሎቹን በዋስ ለቀቋቸው። ወንድሞችም ወዲያው ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዷቸው፤ እነርሱም እዚያ በደረሱ ጊዜ፣ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ። የቤርያ ሰዎች ከተሰሎንቄ ሰዎች ይልቅ አስተዋዮች ስለ ነበሩ፣ “ነገሩ እንደዚህ ይሆንን?” እያሉ መጻሕፍትን በየዕለቱ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጕጕት ተቀብለዋል። ስለዚህ ከእነርሱ ብዙዎቹ አመኑ፤ ደግሞም ከእነርሱ ጋር ቍጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ዕውቅ የግሪክ ሴቶችና ወንዶችም አመኑ። በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድም፣ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል በቤርያ ጭምር መስበኩን ባወቁ ጊዜ፣ ሕዝቡን ለመቀስቀስና ለማነሣሣት ወደዚያ ደግሞ ሄዱ። በዚህ ጊዜ ወንድሞች ጳውሎስን ቶሎ ብለው ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሰደዱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው ቀሩ። ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም አቴና አደረሱት፤ ከዚያም ሲላስና ጢሞቴዎስ ወደ እርሱ በፍጥነት እንዲመጡ የሚል ትእዛዝ ተቀብለው ተመለሱ።
ሐዋርያት ሥራ 17 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 17
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 17:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos