ሐዋርያት ሥራ 17:1-15
ሐዋርያት ሥራ 17:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አንፊጶልና አጶሎንያ ወደሚባሉ ሀገሮችም ሄዱ፤ የአይሁድ ምኵራብ ወደ አለበት ወደ ተሰሎንቄም ደረሱ። ጳውሎስም እንደ አስለመደው ወደ እነርሱ ገብቶ ሦስት ሳምንት ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ሲከራከራቸው ሰነበተ። ክርስቶስ እንዲሞት ከሙታንም ተለይቶ እንዲነሣ፥ እየተረጐመና እየአስተማራቸው፥ “ይህ እኔ የነገርኋችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው” ይል ነበር። ከእነርሱና ከደጋጎች አረማውያንም ብዙ ሰዎች፥ ከታላላቆች ሴቶችም ጥቂቶች ያይደሉ አምነው ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ሆኑ። የማያምኑ አይሁድ ግን ቀኑባቸው፤ ከገበያም ክፉዎች ሰዎችን አምጥተው፥ ሰዎችንም ሰብስበው ሀገሪቱን አወኳት፤ ፈለጓቸውም፤ የኢያሶንን ቤትም በረበሩ፤ ወደ ሕዝቡም ሊያወጧቸው ሽተው ነበር። በአጧቸውም ጊዜ ኢያሶንን ጐተቱት፤ በዚያም የነበሩትን ጓደኞች ጭምር ወደ ሹሞቹ ወሰዱአቸው፤ እየጮኹም እንዲህ ይሉ ነበር፥ “ዓለምን የሚያውኳት እነዚህ ናቸው፤ ወደዚህም መጥተዋል። ይህ ኢያሶንም ተቀበላቸው፤ እነርሱም በቄሣር ላይ የወንጀል ሥራ ይሠራሉ፤ ሌላ ሕግንም ያስተምራሉ፤ ኢየሱስም ሌላ ንጉሥ ነው” ይላሉ። ሕዝቡና የከተማው ሹሞችም ይህን በሰሙ ጊዜ ታወኩ። ከኢያሶንና ከጓደኞቹም ዋስ ተቀብለው ለቀቁአቸው። ወንድሞች ግን ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሸኙአቸው፤ ወደዚያም በደረሱ ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ። በተሰሎንቄ ካሉትም እነርሱ ይሻላሉ፤ በፍጹም ደስታ ቃላቸውን ተቀብለዋልና፤ ነገሩም እንደ አስተማሩአቸው እንደ ሆነ ለመረዳት ዘወትር መጻሕፍትን ይመረምሩ ነበር። ከመካከላቸውም ያመኑ ብዙዎች ነበሩ፤ ከአረማውያን ወገን የሆኑ ብዙ ደጋግ ሴቶችም ነበሩ፤ ወንዶችም ብዙዎች ነበሩ። በተሰሎንቄ የነበሩ አይሁድ ግን ጳውሎስ በቤርያ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ አስተማረ ባወቁ ጊዜ፥ ወደዚያ መጥተው ሕዝቡን አወኩአቸው። ያንጊዜም ወንድሞች ጳውሎስን ሸኝተው ወደ ባሕር አደረሱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን በዚያው ቀሩ። ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም እስከ አቴና ከተማ ድረስ አብረውት መጥተው ነበርና ፈጥነው ይከተሉት ዘንድ ወደ ሲላስና ወደ ጢሞቴዎስ ላካቸው፤ ተመልሰውም ሄዱ።
ሐዋርያት ሥራ 17:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጳውሎስና ሲላስም በአንፊጶልና በአጶሎንያ ዐልፈው ወደ ተሰሎንቄ ሄዱ፤ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበር። ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሦስት ሰንበትም ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነርሱ ጋር ተነጋገረ፤ ክርስቶስ መከራን መቀበል እንዳለበትና ከሙታንም መነሣት እንደሚገባው እያስረዳ በማረጋገጥ፣ “ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው” አላቸው። አይሁድም አንዳንዶቹ የሰሙትን በመቀበል ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤ ደግሞም ቍጥራቸው ብዙ የሆነ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ግሪኮችና አያሌ ዕውቅ ሴቶች የሰሙትን ተቀብለው ከእነርሱ ጋር ተባበሩ። አይሁድ ግን ስለ ቀኑ ወስላቶችን ከገበያ ቦታ አሰባሰቡ፤ ሕዝቡንም አነሣሥተው በከተማው ውስጥ ሁከት ፈጠሩ፤ ጳውሎስንና ሲላስንም አምጥተው ሕዝቡ ፊት ለማቅረብ ወደ ኢያሶን ቤት እየተጣደፉ ሄዱ፤ ነገር ግን ሊያገኟቸው አልቻሉም፤ ስለዚህ ኢያሶንንና ሌሎች ወንድሞችን በከተማው ባለ ሥልጣናት ፊት እየጐተቷቸው እንዲህ እያሉ ጮኹ፤ “እነዚህ ሰዎች ዓለሙን ሁሉ ሲያውኩ ቈይተው፣ አሁን ደግሞ ወደዚህ መጥተዋል፤ ኢያሶንም በቤቱ ተቀብሏቸዋል፤ እነዚህም ሁሉ፣ ‘ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ’ በማለት የቄሳርን ሕግ የሚጥሱ ናቸው።” ሕዝቡና የከተማውም ሹማምት ይህን በሰሙ ጊዜ ተሸበሩ፤ ከዚያም ኢያሶንንና ሌሎቹን በዋስ ለቀቋቸው። ወንድሞችም ወዲያው ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዷቸው፤ እነርሱም እዚያ በደረሱ ጊዜ፣ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ። የቤርያ ሰዎች ከተሰሎንቄ ሰዎች ይልቅ አስተዋዮች ስለ ነበሩ፣ “ነገሩ እንደዚህ ይሆንን?” እያሉ መጻሕፍትን በየዕለቱ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጕጕት ተቀብለዋል። ስለዚህ ከእነርሱ ብዙዎቹ አመኑ፤ ደግሞም ከእነርሱ ጋር ቍጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ዕውቅ የግሪክ ሴቶችና ወንዶችም አመኑ። በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድም፣ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል በቤርያ ጭምር መስበኩን ባወቁ ጊዜ፣ ሕዝቡን ለመቀስቀስና ለማነሣሣት ወደዚያ ደግሞ ሄዱ። በዚህ ጊዜ ወንድሞች ጳውሎስን ቶሎ ብለው ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሰደዱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው ቀሩ። ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም አቴና አደረሱት፤ ከዚያም ሲላስና ጢሞቴዎስ ወደ እርሱ በፍጥነት እንዲመጡ የሚል ትእዛዝ ተቀብለው ተመለሱ።
ሐዋርያት ሥራ 17:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በአንፊጶልና በአጶሎንያም ካለፉ በኋላ ወደ ተሰሎንቄ መጡ፥ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበረ። ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፥ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር፤ ሲተረጉምም ክርስቶስ መከራ እንዲቀበልና ከሙታን እንዲነሣ ይገባው ዘንድ እያስረዳ፦ ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው ይል ነበር። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፥ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ። አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፥ ወደ ሕዝብም ያወጡአቸው ዘንድ ፈልገው ወደ ኢያሶን ቤት ቀረቡ፤ ባላገኙአቸውም ጊዜ ኢያሶንንና ከወንድሞች አንዳንዶችን ወደ ከተማው አለቆች ጎትተው፦ ዓለምን ያወኩ እነዚህ ወደዚህ ደግሞ መጥተዋል፥ ኢያሶንም ተቀብሎአቸዋል፤ እነዚህም ሁሉ፦ ኢየሱስ የሚሉት ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ የቄሣርን ትእዛዝ ይቃወማሉ ብለው ጮኹ። ሕዝቡና የከተማውም አለቆች ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ታወኩ፥ ከኢያሶንና ከሌሎቹም ዋስ ተቀብለው ለቀቁአቸው። ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፥ በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፦ ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ። ስለዚህም ከእነርሱ ብዙ፥ ከግሪኮችም የከበሩት ሴቶችና ወንዶች ጥቂት ያይደሉ፥ አመኑ። በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድ ግን ጳውሎስ በቤርያ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ሰበከ ባወቁ ጊዜ፥ ወደዚያው ደግሞ መጡና ሕዝቡን አወኩ። በዚያን ጊዜም ወንድሞቹ ወዲያው ጳውሎስን እስከ ባሕር ድረስ ይሄድ ዘንድ ሰደዱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስም በዚያው ቀሩ። ጳውሎስን የሸኙት ግን እስከ አቴና አደረሱት፥ እንደሚቻላቸውም በፍጥነት ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ ወደ ሲላስና ወደ ጢሞቴዎስ ትእዛዝ ተቀብለው ሄዱ።
ሐዋርያት ሥራ 17:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጳውሎስና ሲላስ በአንፊጶሊስና በአጶሎንያ አልፈው ወደ ተሰሎንቄ ሄዱ፤ እዚያም የአይሁድ ምኲራብ ነበረ። ጳውሎስ እንደ ልማዱ ወደ ምኲራብ ገባ፤ ለሦስት ሰንበትም አከታትሎ ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ለሕዝብ ያስረዳ ነበር። መሲሕ መከራ መቀበልና ከሞት መነሣት እንደሚገባው ገልጦ እያስረዳ “ይህ እኔ የማበሥራችሁ ኢየሱስ መሲሕ ነው” ይል ነበር። ስለዚህ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ቃሉን ተረድተው ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤ እንዲሁም እግዚአብሔርን የሚያመልኩ እጅግ ብዙ አሕዛብ በከተማው የታወቁ ብዙ ሴቶች ቃሉን ተረድተው ተባበሩ። አይሁድ ግን ቀንተው የሚበጠብጡ ሥራ ፈቶችን ከየመንገዱ ሰበሰቡና አሳደሙ። በከተማው ውስጥ ብጥብጥ እንዲነሣ አደረጉ፤ ጳውሎስንና ሲላስን አውጥተው ለሕዝቡ ለመስጠትም የኢያሶንን ቤት ከበቡ። ነገር ግን እነርሱን ባጡአቸው ጊዜ ኢያሶንንና አንዳንድ አማኞችን ለከተማው ባለሥልጣኖች ለማቅረብ እየጐተቱ ወሰዱአቸው፤ እንዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ “እነዚህ ዓለምን ሁሉ ያወኩ ሰዎች አሁን ደግሞ ወደዚህ መጥተዋል! ኢያሶንም ተቀብሎአቸዋል፤ ‘ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ’ እያሉም የሮምን ንጉሠ ነገሥት ትእዛዝ ይቃወማሉ።” ሕዝቡና የከተማው ባለሥልጣኖች ይህን በሰሙ ጊዜ ተሸበሩ። ኢያሶንንና ሌሎቹንም ዋስ አስጠርተው ለቀቁአቸው። ወንድሞች በቶሎ ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ እንዲሄዱ አደረጉአቸው፤ እዚያም በደረሱ ጊዜ ወደ አይሁድ ምኲራብ ገቡ። በቤርያ ያሉት አይሁድ በተሰሎንቄ ካሉት ይልቅ ቅን አመለካከት ያላቸው ስለ ነበሩ ቃሉን በታላቅ ደስታ ተቀበሉ፤ የቃሉንም እውነተኛነት ለማረጋገጥ በየቀኑ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይመረምሩ ነበር። ስለዚህ ከእነርሱ ብዙዎች አመኑ፤ ብዙዎች የግሪክ ሀብታሞች ሴቶችና ብዙዎች ግሪካውያን ወንዶችም አመኑ። ነገር ግን በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድ ጳውሎስ በቤርያም የእግዚአብሔርን ቃል እንዳበሠረ ባወቁ ጊዜ ወደዚያ መጡና ሕዝቡን አሳድመው ብጥብጥ አስነሡ። በዚህ ጊዜ ወንድሞች በቶሎ ጳውሎስ ወደ ባሕሩ አጠገብ እንዲሄድ አደረጉት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው በቤርያ ቀሩ። ጳውሎስን የሸኙት ሰዎች እስከ አቴና አደረሱት “ሲላስና ጢሞቴዎስ ሳይዘገዩ በቶሎ ወደ እኔ ይምጡልኝ” የሚለውንም የጳውሎስን ትእዛዝ ይዘው ወደ ቤርያ ተመለሱ።
ሐዋርያት ሥራ 17:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በአንፊጶሊስና በአጶሎንያም ካለፉ በኋላ ወደ ተሰሎንቄ መጡ፤ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበረ። ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፤ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር፤ ሲተረጉምም ክርስቶስ መከራ እንዲቀበልና ከሙታን እንዲነሣ ይገባው ዘንድ እያስረዳ “ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው፤” ይል ነበር። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፥ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ። አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፤ ወደ ሕዝብም ያወጡአቸው ዘንድ ፈልገው ወደ ኢያሶን ቤት ቀረቡ፤ ባላገኙአቸውም ጊዜ ኢያሶንንና ከወንድሞች አንዳንዶችን ወደ ከተማው አለቆች ጎትተው “ዓለምን ያወኩ እነዚህ ወደዚህ ደግሞ መጥተዋል፥ ኢያሶንም ተቀብሎአቸዋል፤ እነዚህም ሁሉ ‘ኢየሱስ የሚሉት ሌላ ንጉሥ አለ፤’ እያሉ የቄሣርን ትእዛዝ ይቃወማሉ፤” ብለው ጮኹ። ሕዝቡና የከተማውም አለቆች ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ታወኩ፤ ከኢያሶንና ከሌሎቹም ዋስ ተቀብለው ለቀቁአቸው። ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፤ በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና “ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን?” ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ። ስለዚህም ከእነርሱ ብዙ፥ ከግሪኮችም የከበሩት ሴቶችና ወንዶች ጥቂት ያይደሉ አመኑ። በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድ ግን ጳውሎስ በቤርያ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሰበከ ባወቁ ጊዜ፥ ወደዚያው ደግሞ መጡና ሕዝቡን አወኩ። በዚያን ጊዜም ወንድሞች ወዲያው ጳውሎስን እስከ ባሕር ድረስ ይሄድ ዘንድ ሰደዱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስም በዚያው ቀሩ። ጳውሎስን የሸኙት ግን እስከ አቴና አደረሱት፤ እንደሚቻላቸውም በፍጥነት ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ ወደ ሲላስና ወደ ጢሞቴዎስ ትእዛዝ ተቀብለው ሄዱ።