ሐዋርያት ሥራ 17
17
ጳውሎስና ሲላስ በተሰሎንቄ
1ጳውሎስና ሲላስም በአንፊጶልና በአጶሎንያ ዐልፈው ወደ ተሰሎንቄ ሄዱ፤ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበር። 2ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሦስት ሰንበትም ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነርሱ ጋር ተነጋገረ፤ 3ክርስቶስ#17፥3 ወይም መሲሕ መከራን መቀበል እንዳለበትና ከሙታንም መነሣት እንደሚገባው እያስረዳ በማረጋገጥ፣ “ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው” አላቸው። 4አይሁድም አንዳንዶቹ የሰሙትን በመቀበል ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤ ደግሞም ቍጥራቸው ብዙ የሆነ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ግሪኮችና አያሌ ዕውቅ ሴቶች የሰሙትን ተቀብለው ከእነርሱ ጋር ተባበሩ።
5አይሁድ ግን ስለ ቀኑ ወስላቶችን ከገበያ ቦታ አሰባሰቡ፤ ሕዝቡንም አነሣሥተው በከተማው ውስጥ ሁከት ፈጠሩ፤ ጳውሎስንና ሲላስንም አምጥተው ሕዝቡ ፊት#17፥5 ወይም በሕዝብ ጉባኤ ፊት ለማቅረብ ወደ ኢያሶን ቤት እየተጣደፉ ሄዱ፤ 6ነገር ግን ሊያገኟቸው አልቻሉም፤ ስለዚህ ኢያሶንንና ሌሎች ወንድሞችን በከተማው ባለ ሥልጣናት ፊት እየጐተቷቸው እንዲህ እያሉ ጮኹ፤ “እነዚህ ሰዎች ዓለሙን ሁሉ ሲያውኩ ቈይተው፣ አሁን ደግሞ ወደዚህ መጥተዋል፤ 7ኢያሶንም በቤቱ ተቀብሏቸዋል፤ እነዚህም ሁሉ፣ ‘ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ’ በማለት የቄሳርን ሕግ የሚጥሱ ናቸው።” 8ሕዝቡና የከተማውም ሹማምት ይህን በሰሙ ጊዜ ተሸበሩ፤ 9ከዚያም ኢያሶንንና ሌሎቹን በዋስ ለቀቋቸው።
ጳውሎስና ሲላስ በቤርያ
10ወንድሞችም ወዲያው ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዷቸው፤ እነርሱም እዚያ በደረሱ ጊዜ፣ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ። 11የቤርያ ሰዎች ከተሰሎንቄ ሰዎች ይልቅ አስተዋዮች ስለ ነበሩ፣ “ነገሩ እንደዚህ ይሆንን?” እያሉ መጻሕፍትን በየዕለቱ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጕጕት ተቀብለዋል። 12ስለዚህ ከእነርሱ ብዙዎቹ አመኑ፤ ደግሞም ከእነርሱ ጋር ቍጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ዕውቅ የግሪክ ሴቶችና ወንዶችም አመኑ።
13በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድም፣ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል በቤርያ ጭምር መስበኩን ባወቁ ጊዜ፣ ሕዝቡን ለመቀስቀስና ለማነሣሣት ወደዚያ ደግሞ ሄዱ። 14በዚህ ጊዜ ወንድሞች ጳውሎስን ቶሎ ብለው ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሰደዱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው ቀሩ። 15ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም አቴና አደረሱት፤ ከዚያም ሲላስና ጢሞቴዎስ ወደ እርሱ በፍጥነት እንዲመጡ የሚል ትእዛዝ ተቀብለው ተመለሱ።
ጳውሎስ በአቴና
16ጳውሎስ በአቴና ሆኖ ሲጠብቃቸው ሳለ፣ ከተማዪቱ በጣዖት የተሞላች መሆኗን በማየት መንፈሱ ተበሳጨበት። 17ስለዚህ በምኵራብ ሆኖ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ግሪኮች ጋር፣ ደግሞም በገበያ ስፍራ ዕለት ዕለት ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይነጋገር ነበር። 18ከኤፊቆሮስና ከኢስጦኢክ የፍልስፍና ወገን የሆኑትም ወደ እርሱ መጥተው ይከራከሩት ነበር። አንዳንዶቹ፣ “ይህ ለፍላፊ ምን ለማለት ይፈልጋል?” ይሉ ነበር፤ ሌሎች ደግሞ ስለ ኢየሱስና ስለ ትንሣኤው የምሥራች ሲሰብክ ሰምተው፣ “ስለ አዳዲስ ባዕዳን አማልክት የሚናገር ይመስላል” አሉ። 19ይዘውም አርዮስፋጎስ ወደተባለው ስፍራ በመውሰድ እንዲህ አሉት፤ “አንተ የምታስተምረው ይህ አዲስ ትምህርት ምን እንደ ሆነ እንድናውቅ ትፈቅዳለህን? 20ደግሞም በጆሯችን የምታሰማን እንግዳ ነገር ስለ ሆነብን፣ ምን ማለት እንደ ሆነ ማወቅ እንፈልጋለን።” 21የአቴና ሰዎች በሙሉ እንዲሁም በዚያ የሚኖሩ የውጭ ሰዎች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ስለ አዳዲስ ነገሮች በማውራትና በመስማት እንጂ በሌላ ጕዳይ አልነበረም።
22ስለዚህ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፤ “የአቴና ሰዎች ሆይ፤ በማናቸውም ረገድ፣ በጣም ሃይማኖተኞች መሆናችሁን አያለሁ፤ 23እየተዘዋወርሁ ሳለሁ፣ የምታመልኳቸውን ነገሮች ስመለከት፣ ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሑፍ ያለበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁና፤ እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ።
24“ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነው፤ ስለዚህም እርሱ የሰው እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም። 25እርሱ ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም። 26የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን ፈጥሮ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ አደረገ፤ የዘመናቸውን ልክና የመኖሪያ ስፍራቸውንም ዳርቻ ወሰነላቸው። 27ይኸውም ሰዎች እግዚአብሔርን ፈልገው ተመራምረው ምናልባት ያገኙት እንደ ሆነ ብሎ ነው፤ ይህም ቢሆን እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ሆኖ አይደለም፤ 28የምንኖረውና የምንንቀሳቀሰው፣ ያለነውም በእርሱ ነውና። ከራሳችሁ ባለቅኔዎችም አንዳንዶቹ እንዳሉት፣ ‘እኛም ደግሞ ልጆቹ ነን።’
29“እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን፣ አምላክ በሰው ሙያና ጥበብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ ይመስላል ብለን ማሰብ አይገባንም። 30ቀደም ሲል እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን አለማወቅ በትዕግሥት ዐልፏል፤ አሁን ግን በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ ያዝዛል። 31በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኗልና፤ እርሱንም ከሙታን በማስነሣቱ ለሰዎች ሁሉ ይህን አረጋግጧል።”
32እነርሱም ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ፣ አንዳንዶቹ አፌዙ፤ ሌሎች ግን፣ “ስለዚህ ጕዳይ ከአንተ ዳግመኛ ለመስማት እንፈልጋለን” አሉት። 33በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጥቶ ሄደ፤ 34አንዳንድ ሰዎች ግን ጳውሎስ ባለው በመስማማት ተከተሉት፤ አመኑም፤ ከእነዚህም ዲዮናስዮስ የተባለው የአርዮስፋጎስ ፍርድ ቤት አባል፣ ደማሪስ የተባለች ሴትና ሌሎችም ሰዎች ነበሩ።
Currently Selected:
ሐዋርያት ሥራ 17: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.