ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት ከማረኩ በኋላ፣ ከአቤንኤዘር ወደ አሽዶድ ወሰዱት። ከዚያም ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ዳጎን ቤተ ጣዖት አግብተው፣ በዳጎን አጠገብ አኖሩት። የአሽዶድም ሰዎች በማግስቱም ማለዳ ተነሥተው ሲመለከቱ እነሆ፣ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት። ከዚያም አንሥተው ወደ ቦታው መለሱት። በሚቀጥለው ቀን ጧት ተነሥተው ሲመለከቱ፣ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት፣ መሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ ነበር፤ ራሱና እጆቹ ተሰባብረው በደጃፉ ላይ የወደቁ ሲሆን፣ የቀረው ሌላው አካሉ ብቻ ነበር። የዳጎን ካህናትም ሆኑ ሌሎች በአሽዶድ ወዳለው የዳጎን ቤተ ጣዖት የሚገቡ ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ እግራቸው ደጃፉን እንዳይረግጥ ተራምደው የሚያልፉት በዚሁ ምክንያት ነው። የእግዚአብሔር እጅ በአሽዶድ ሕዝብና በአካባቢዋ ላይ ጠነከረ፤ እርሱም ጥፋት አመጣባቸው፤ በዕባጭም መታቸው። የአሽዶድ ሰዎች ይህን ባዩ ጊዜ፣ “እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክሯልና የእስራኤል አምላክ ታቦት በእኛ ዘንድ መቈየት የለበትም” አሉ። ከዚህ በኋላ የፍልስጥኤማውያንን ገዦች በሙሉ ጠርተው፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ምን እናድርገው?” ሲሉ ጠየቁ። እነርሱም፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወደ ጋት ውሰዱት” አሏቸው። ስለዚህ የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወሰዱት። ነገር ግን ታቦቱን ወደዚያ ከወሰዱት በኋላ የእግዚአብሔር እጅ በከተማዪቱ ላይ ሆነ፤ ታላቅ መሸበርም አመጣባቸው፤ ሕፃን ሽማግሌ ሳይል ሕዝቡን በዕባጭ መታ። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ አቃሮን ሰደዱት። የእግዚአብሔር ታቦት እዚያ ሲገባም፣ የአቃሮን ሕዝብ፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ያመጡብን እኛንና ሕዝባችንን ለማስፈጀት ነው” በማለት ጮኹ። የእግዚአብሔር እጅ በርትቶባቸው ስለ ነበር፣ ሞት ከተማዪቱን እጅግ አስደንግጧት ነበርና ሕዝቡ የፍልስጥኤማውያንን ገዦች በሙሉ ጠርተው፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ከዚህ አርቁልን፤ ወደ ገዛ ስፍራው ይመለስ፤ አለዚያ እኛንም ሕዝባችንንም ይፈጃል” አሉ። ያልሞቱትን ደግሞ ዕባጩ ያሠቃያቸው ስለ ነበር፣ የከተማዪቱ ጩኸት እስከ ሰማይ ወጣ።
1 ሳሙኤል 5 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ሳሙኤል 5
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ሳሙኤል 5:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች