ፍልስጥኤማውያን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከማረኩ በኋላ ከአቤንዔዜር አሽዶድ ተብላ ወደምትጠራ ከተማቸው ወሰዱአት። ዳጎን ተብሎ ወደሚጠራውም አምላካቸው ቤተ ጣዖት አስገቡት፤ ከምስሉም ሐውልት ጐን አቆሙት። በማግስቱም ማለዳ የአሽዶድ ሰዎች ተነሥተው ሲመለከቱ የዳጎን ምስል ሐውልት በእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ፊት በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ አዩት፤ ከዚያም አንሥተው ቀድሞ በነበረበት ስፍራ አቆሙት፤ በተከታዩም ቀን ማለዳ ተነሥተው ሲመለከቱ የምስሉ ሐውልት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት እንደገና ወድቆ አዩት፤ በዚህ ጊዜ ራሱና ሁለት እጆቹ ተሰባብረው በመግቢያው መድረክ ላይ ወድቀው ሌላው አካሉ ብቻ ቀርቶ ነበር። ዛሬም እንኳ ቢሆን የዳጎን ካህናትና በአሽዶድ እርሱን የሚያመልኩት ሁሉ ያን የመግቢያ መድረክ በእግራቸው ሳይረግጡ ተራምደው የሚሄዱበት ምክንያት ይኸው ነው። እግዚአብሔርም የአሽዶድን ሕዝብ በብርቱ አስጨነቃቸው፤ እነርሱንና በዙሪያቸው ያሉትን ሕዝብ ሁሉ በእባጭ መቅሠፍት ቀጣቸው። የአሽዶድ ኗሪዎች የሆነውን ነገር ሁሉ ባዩ ጊዜ “ቊጣው በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ስለ በረታ የእስራኤል አምላክ ታቦት እዚህ እኛ ዘንድ መቈየት የለበትም” አሉ። በዚህም ምክንያት ወደ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን ነገሥታት መልእክተኞች ልከው በማስጠራት “ስለ እስራኤል አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት ምን እናድርግ” ብለው ጠየቁአቸው። እነርሱም “ወደ ጋት ውሰዱት” ብለው መለሱላቸው፤ ስለዚህም ጋት ተብላ ወደምትጠራው ወደ ሌላይቱ የፍልስጥኤማውያን ከተማ ወሰዱት፤ ነገር ግን የቃል ኪዳኑ ታቦት እዚያ ከደረሰ በኋላ እግዚአብሔር ያቺንም ከተማ ጭምር ቀጣ፤ ሕዝብዋንም በብርቱ አስጨነቀ። ሕፃኑንም ሽማግሌውንም ሳይለይ ሕዝቡን ሁሉ በአንድነት በእብጠት በሽታ ቀጣቸው፤ ስለዚህም የቃል ኪዳኑ ታቦት ዔቅሮን ተብላ ወደምትጠራው ወደ ሌላይቱ የፍልስጥኤማውያን ከተማ እንዲወሰድ አደረጉ፤ ነገር ግን እዚያ በደረሰ ጊዜ ኗሪዎቹ እየጮኹ በማልቀስ “የእስራኤልን አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት ወደዚህ ያመጡብን እኛን ሁላችንን ለመፍጀት አስበው ነው!” አሉ። እንደገና ወደ ፍልስጥኤማውያን ነገሥታት ሁሉ መልእክተኞች ልከው “እኛንና ቤተሰባችንን ሁሉ ከመፍጀቱ በፊት የእስራኤልን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ስፍራው መልሳችሁ ላኩ” አሉ፤ እግዚአብሔር በብርቱ ስለ ቀጣቸው በመላ ከተማይቱ የሚያስጨንቅ የሞት ፍርሀት ነበር፤ ከሞት የተረፉትም የእባጩ በሽታ በርትቶባቸው ስለ ነበር ሕዝቡ ርዳታ ለማግኘት ወደ አማልክታቸው በማልቀስ ጮኹ።
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 5:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች