1 ሳሙኤል 5
5
ታቦቱ ወደ አሽዶድና ወደ አቃሮን ተወሰደ
1ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት ከማረኩ በኋላ፣ ከአቤንኤዘር ወደ አሽዶድ ወሰዱት። 2ከዚያም ወደ ዳጎን ቤተ ጣዖት አግብተው፣ በዳጎን አጠገብ አኖሩት። 3የአሽዶድም ሰዎች በማግስቱም ማለዳ ተነሥተው ሲመለከቱ እነሆ፣ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት። ከዚያም አንሥተው ወደ ቦታው መለሱት። 4በሚቀጥለው ቀን ጧት ተነሥተው ሲመለከቱ፣ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት፣ መሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ ነበር፤ ራሱና እጆቹ ተሰባብረው በደጃፉ ላይ የወደቁ ሲሆን፣ የቀረው ሌላው አካሉ ብቻ ነበር። 5የዳጎን ካህናትም ሆኑ ሌሎች በአሽዶድ ወዳለው የዳጎን ቤተ ጣዖት የሚገቡ ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ እግራቸው ደጃፉን እንዳይረግጥ ተራምደው የሚያልፉት በዚሁ ምክንያት ነው።
6 የእግዚአብሔር እጅ በአሽዶድ ሕዝብና በአካባቢዋ ላይ ጠነከረ፤ እርሱም ጥፋት አመጣባቸው፤ በዕባጭም መታቸው#5፥6 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናት የቩልጊት ትርጕም ግን በምድራቸው ላይ ዐይጥ መታየት ጀመረ፤ እንዲሁም ሞትና ጥፋት በከተማዪቱ ዙሪያ ነበር ይላል።። 7የአሽዶድ ሰዎች ይህን ባዩ ጊዜ፣ “እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክሯልና የእስራኤል አምላክ ታቦት በእኛ ዘንድ መቈየት የለበትም” አሉ። 8ከዚህ በኋላ የፍልስጥኤማውያንን ገዦች በሙሉ ጠርተው፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ምን እናድርገው?” ሲሉ ጠየቁ።
እነርሱም፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወደ ጌት ውሰዱት” አሏቸው። ስለዚህ የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወሰዱት።
9ነገር ግን ታቦቱን ወደዚያ ከወሰዱት በኋላ የእግዚአብሔር እጅ በከተማዪቱ ላይ ሆነ፤ ታላቅ መሸበርም አመጣባቸው፤ ሕፃን ሽማግሌ ሳይል ሕዝቡን በዕባጭ መታ#5፥9 ወይም ብልታቸውን አሳበጠባቸው። 10ስለዚህ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ አቃሮን ሰደዱት።
የእግዚአብሔር ታቦት እዚያ ሲገባም፣ የአቃሮን ሕዝብ፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ያመጡብን እኛንና ሕዝባችንን ለማስፈጀት ነው” በማለት ጮኹ። 11የእግዚአብሔር እጅ በርትቶባቸው ስለ ነበር፣ ሞት ከተማዪቱን እጅግ አስደንግጧት ነበርና ሕዝቡ የፍልስጥኤማውያንን ገዦች በሙሉ ጠርተው፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ከዚህ አርቁልን፤ ወደ ገዛ ስፍራው ይመለስ፤ አለዚያ እኛንም ሕዝባችንንም ይፈጃል” አሉ። 12ያልሞቱትን ደግሞ ዕባጩ ያሠቃያቸው ስለ ነበር፣ የከተማዪቱ ጩኸት እስከ ሰማይ ወጣ።
Currently Selected:
1 ሳሙኤል 5: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.