የዮሐንስ ወንጌል 6

6
ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን እንደመገበ
(ማቴ. 14፥13-21ማር. 6፥30-44ሉቃ. 9፥10-17)
1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ፤ እርሱም የጥብርያዶስ ባሕር ነው። 2በበሽተኞችም ያደረገውን ምልክቶች ስላዩ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። 3ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። 4የአይሁድ በዓል ፋሲካም ቀርቦ ነበር። 5ኢየሱስም ዐይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን “እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን?” አለው። 6ሊፈትነው ይህን ተናገረ፤ እራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና። 7ፊልጶስ “እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም፤” ብሎ መለሰለት። 8ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ እንዲህ አለው፦ 9“አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን ለዚህ ሁሉ ሰው ምን ይሆናል?” 10ኢየሱስም “ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ፤” አለ። በዚያም ስፍራ ብዙ ሣር ነበረበት። ወንዶችም ተቀመጡ፤ ቁጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር። 11ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ፤ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው፤ እንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን። 12ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “አንድም እንኳን እንዳይጠፋ የተረፈውን ቁርስራሽ አከማቹ፤” አላቸው። 13ሰለዚህም አከማቹ፤ ከበሉትም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ። 14ከዚህ የተነሣ ሰዎቹ ኢየሱስ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው፤” አሉ።
15ኢየሱስም መጥተው በጉልበት ሊያነግሡት መሆናቸውን አውቆ በድጋሚ ወደ ተራራ ለብቻው ርቆ ሄደ።
ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ እንደ ሄደ
(ማቴ. 14፥22-23ማር. 6፥45-52)
16በመሸም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ፤ 17በታንኳም ገብተው በባሕር ማዶ ወደ ቅፍርናሆም ይመጡ ነበር። ከወዲሁ ጨልሞ ነበር፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር፤ 18ብርቱ ነፋስም ስለ ነፈሰ ባሕሩ ተናወጠ። 19ሃያ አምስት ወይም ሠላሳ ምዕራፍ#6፥19 አምስት ወይም ስድስት ኪሎ ሜትር እንደማለት ነው። ከቀዘፉ በኋላም፥ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ ታንኳይቱ ሲቀርብ አይተው ፈሩ። 20እርሱ ግን “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፤” አላቸው። 21ስለዚህ በታንኳይቱ ሊቀበሉት ወደዱ፤ ወዲያውም ታንኳይቱ ወደሚሄዱበት ምድር ደረሰች።
የሕይወት እንጀራ
22በማግሥቱም በባሕር ማዶ ቆሞ የነበረው ሕዝብ ከአንዲት ጀልባ በቀር በዚያ ሌላ ጀልባ እንዳልነበረች፥ ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው እንደ ሄዱ እንጂ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ እንዳልገባ አዩ፤ 23ዳሩ ግን ሌሎች ጀልባዎች ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በሉበት ስፍራ አጠገብ ከጥብርያዶስ መጡ። 24ሕዝቡም ኢየሱስ ወይም ደቀመዛሙርቱ በዚያ እንዳልነበሩ ባዩ ጊዜ፥ እራሳቸው በጀልባዎቹ ገብተው ኢየሱስን እየፈለጉ ወደ ቅፍርናሆም መጡ።
25በባሕር ማዶም ሲያገኙት “መምህር ሆይ! ወደዚህ መቼ መጣህ?” አሉት። 26ኢየሱስም መልሶ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። 27#ሲራ. 24፥19-22።ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን የለዘለዓለም ሕይወት ለሚሆነው መብል ሥሩ፤ ይህም የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ነው፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።” 28እንግዲህ “የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን እናድርግ?” አሉት። 29ኢየሱስ መልሶ “የእግዚአብሔር ሥራ ይህ ነው፤ ይህም እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው፤” አላቸው። 30እንዲህም አሉት፦ “ታዲያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ዓይነት ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? 31#ዘፀ. 16፥4፤15፤ መዝ. 78፥24፤ ጥበ. 16፥20፤21።‘ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው፤’ ተብሎ እንደ ተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ፤” አሉት። 32ኢየሱስም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ 33የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና፤” አላቸው። 34ስለዚህ “ጌታ ሆይ! ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን፤” አሉት።
35ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔ የሚያምንም በፍጹም አይጠማም። 36ነገር ግን እንዳያችሁኝ፥ እንዳላመናችሁም ነገርኳችሁ። 37አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላስወጣውም፤ 38ፈቃዴን ለማድረግ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና። 39የላከኝ የአብ ፈቃድም ይህ ነው፤ ከሰጠኝ ሁሉ አንድም እንኳን እንዳላጠፋ፥ ይልቁንም በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው ነው። 40የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፤ ወልድን አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።”
41አይሁድም “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ፤” በማለቱ ማንጐራጐር ጀመሩ፤ 42“ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? አባቱንና እናቱን እናውቃቸው የለምን? ታዲያ ‘ከሰማይ ወርጃለሁ’ እንዴት ይላል?” አሉ። 43ኢየሱስም መለሰ፥ አላቸውም፦ “እርስ በእርሳችሁ አታንጐራጉሩ። 44የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚችል የለም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። 45#ኢሳ. 54፥13።‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤’ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማና የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። 46አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነው በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል። 47እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው። 48እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ። 49አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ሞቱም፤ 50ሰው ከእርሱ እንዲበላ፥ እናም እንዳይሞት ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው። 51እኔ ከሰማይ የወረደው ሕያው እንጀራ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።”
52አይሁድም “ይህ ሰው ሥጋውን እንድንበላ እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። 53ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ#6፥53 የክርስቶስን ማለት ነው። ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በእራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። 54ሥጋዬን የሚበላ፥ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። 55ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። 56ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። 57ሕያው አብ እንደ ላከኝ፥ እኔም በአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚመገበኝ ደግሞ በእኔ ሕያው ይሆናል። 58ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ በልተው ነገር ግን እንደሞቱበት ዓይነት አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል።” 59በቅፍርናሆም፥ በምኵራብ ሲያስተምር ነበር ይህን ያለው።
የዘለዓለም ሕይወት ቃል
60ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ በሰሙ ጊዜ “ይህ ንግግር ከባድ ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ። 61ኢየሱስ ግን ደቀመዛሙርቱ በዚህ ምክንያት እንዳንጐራጐሩ በልቡ አውቆ እንዲህ አላቸው “ይህ ያስናክላችኋልን? 62ታዲያ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ሊሆን ነው? 63#ጥበ. 9፥13-18።ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋስ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው፤ ሕይወትም ነው። 64ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ።” ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ፥ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደሆነ ከመጀመሪያው ያውቅ ነበርና። 65እንዲህም አለ፦ “ስለዚህ አልኋችሁ፤ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ ያልኋችሁ በዚህ ምክንያት ነው።”
66በዚህም ምክንያት ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደፊትም ከእርሱ ጋር ወደ ፊት መሄድም አቆሙ። 67ኢየሱስም ለዐሥራ ሁለቱ “እናንተም መሄድ ትፈልጋላችሁን?” አለ። 68#ማቴ. 16፥16፤ ማር. 8፥29፤ ሉቃ. 9፥20።ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል አለህ፤ 69እኛስ አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆንህ አምነናል፤ አውቀናልም፤” ብሎ መለሰለት። 70ኢየሱስም “እኔ እናንተን ዐሥራ ሁለታችሁን መርጫችሁ የለምን? ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው፤” ብሎ መለሰላቸው። 71ስለ ስምዖን ልጅ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ መናገሩ ነበር፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ሲሆን፥ አሳልፎም የሚሰጠው እርሱ ነበርና ነው።

Айни замон обунашуда:

የዮሐንስ ወንጌል 6: መቅካእኤ

Лаҳзаҳои махсус

Паҳн кунед

Нусха

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in