የዮሐንስ ወንጌል 5
5
ኢየሱስ በሰንበት አንድ ሽባ ሰው እንደ ፈወሰ
1ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 2በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። 3በእነዚህም ውስጥ ብዙ ድኩማን፥ ዐይነ ሥውሮች፥ አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሰዎች ይተኙ ነበር። 4አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውሃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውሃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ይፈወስ ይሆን ነበር። 5በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ 6ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው። 7ሕመምተኛውም “ጌታ ሆይ! ውሃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ በመምጣት ላይ እያለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል፤” ብሎ መለሰለት። 8ኢየሱስ “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤” አለው። 9ወዲያውም ሰውዬው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ያም ቀን ሰንበት ነበረ።
10 #
ነህ. 13፥19፤ ኤር. 17፥21። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው “ሰንበት ነው፥ አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም፤” አሉት። 11እርሱ ግን “ያዳነኝ ያ ሰው ‘አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤’ አለኝ፤” ብሎ መለሰላቸው። 12እነርሱም “‘አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤’ ያለህ ሰው ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። 13ዳሩ ግን የተፈወሰው ሰው ማን እንደሆነ አላወቀም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ስለ ነበርና፥ በዚያ ስፍራ ብዙ ሰዎች ሰለ ነበሩ ነው። 14ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ አገኘውና “እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ፤” አለው። 15ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደሆነ ለአይሁድ ነገረ። 16ስለዚህም አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር፤ በሰንበት ይህን አድርጎ ነበርና። 17ኢየሱስ ግን “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ፤” ብሎ መለሰላቸው። 18#ጥበ. 2፥16።እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ደግሞ እራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ “እግዚአብሔር አባቴ ነው፤” ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር።
የእግዚአብሔር ልጅ ሥልጣን
19ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ፤ እንዲህም አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከእራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። 20አብ ወልድን ይወዳልና፤ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። 21አብ ሙታንን እንደሚያስነሣቸው፥ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። 22አብ ከቶ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ይልቁንም፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው። 23ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም። 24እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።
25“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። 26አብ በእራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በእራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና። 27የሰው ልጅም#5፥27 ዳን 7፥13ን ይመልከቱ። ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። 28በዚህ አታድንቁ፤ በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ 29#ዳን. 12፥2።መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና።
ስለ ኢየሱስ የተሰጠ ምስክርነት
30“እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ፤ ፍርዴም ቅን ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና። 31እኔ ለእራሴ ብመሰክር ምስክርነቴ እውነት አይደለም፤ 32ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፤ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክር እውነት እንደሆነ አውቃለሁ። 33#ዮሐ. 1፥19-27፤ 3፥27-30።እናንተ ወደ ዮሐንስ መልክተኞችን ልካችኋል፥ እርሱም ለእውነት መስክሮአል። 34እኔ ግን የሰው ምስክር የሚያስፈልገኝ አይደለሁም፤ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ። 35#ሲራ. 48፥1።እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፤ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ። 36እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ እንድፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና። 37#ማቴ. 3፥17፤ ማር. 1፥11፤ ሉቃ. 3፥22።የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤ 38እርሱ የላከውንም እናንተ አታምኑምና፤ በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም። 39#ባሮክ 4፥1።እናንተ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ በእነርሱም የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችሁ ታስባላችሁና፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ 40ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። 41የሰው ክብር አያስፈልገኝም፤ 42ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጣችሁ እንደሌላችሁ ዐወቅሁ። 43እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ፤ አትቀበሉኝምም፤ ሌላው በእራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ። 44እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ፥ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ብቻ የሚገኘውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? 45እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉበት ሙሴ ነው። 46ሙሴንስ ብታምኑት እኔንም ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። 47የእርሱን ጽሑፎች ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?”
Айни замон обунашуда:
የዮሐንስ ወንጌል 5: መቅካእኤ
Лаҳзаҳои махсус
Паҳн кунед
Нусха
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in