ኦሪት ዘፍጥረት 37
37
ዮሴፍና ወንድሞቹ
1ያዕቆብ ተቀማጭነቱን አባቱ በኖረበት በከነዓን ምድር አደረገ። 2የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤
ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረበት ጊዜ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዚልፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር፤ ወንድሞቹ የሚፈጽሙትንም በደል እያመጣ ለአባቱ ይነግር ነበር።
3በስተርጅና የወለደው ስለ ሆነ ያዕቆብ ዮሴፍን ከሌሎች ልጆች ሁሉ አብልጦ ይወደው ነበር፤ ስለዚህም ጌጠኛ የሆነ እጀ ጠባብ ሰፋለት። 4ወንድሞቹም አባታቸው ከእነርሱ ይልቅ ዮሴፍን እንደሚወድ ባዩ ጊዜ በመቅናት ጠሉት፤ መልካም ቃልም ሊናገሩት አልወደዱም።
5አንድ ሌሊት ዮሴፍ ሕልም አየ፤ ሕልሙን ለወንድሞቹ በነገራቸውም ጊዜ ከቀድሞው ይበልጥ ጠሉት። 6እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ፤ 7እኛ ሁላችን በእርሻ ውስጥ የስንዴ ነዶ እናስር ነበር፤ የእኔ ነዶ ተነሣና ቀጥ ብሎ ቆመ፤ የእናንተ ነዶዎች ዙሪያውን ተሰብስበው ለእኔ ነዶ ሰገዱለት።”
8ወንድሞቹም “ታዲያ በእኛ ላይ ንጉሥ ሆነህ ልትገዛን ታስባለህን?” ብለው ጠየቁት። ስላየው ሕልምና ስለ ተናገረው ቃል ከበፊቱ ይበልጥ ጠሉት።
9ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ሌላ ሕልም አይቶ ወንድሞቹን “እነሆ፥ ሌላ ሕልም አየሁ፤ በሕልሜም ፀሐይ፥ ጨረቃና ዐሥራ አንድ ከዋክብት ሰገዱልኝ” አላቸው።
10ይህንኑ ለወንድሞቹ የነገራቸውን ሕልም ለአባቱም በነገረው ጊዜ፥ አባቱ “ይህ ምን ዐይነት ሕልም ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም የምንሰግድልህ ይመስልሃልን?” በማለት ገሠጸው። 11የዮሴፍ ወንድሞች እጅግ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ይህን ነገር በልቡ እያሰላሰለ ይጠብቀው ነበር። #ሐ.ሥ. 7፥9።
ወንድሞቹ ዮሴፍን መሸጣቸው
12አንድ ቀን የዮሴፍ ወንድሞች የአባታቸውን መንጋዎች ይዘው ወደ ሴኬም ተሰማሩ፤ 13እስራኤልም ዮሴፍን “እነሆ፥ ወንድሞችህ መንጋውን ይዘው ወደ ሴኬም መሰማራታቸውን ታውቃለህ፤ ስለዚህ ወደ እነርሱ ልልክህ እፈልጋለሁ” አለው።
ዮሴፍም “እሺ እሄዳለሁ” አለ።
14አባቱም “በል እንግዲህ ሂድና የወንድሞችህንና የመንጋዎቹን ደኅንነት አይተህ ንገረኝ” አለው። በዚህ ዐይነት እስራኤል ዮሴፍን ከኬብሮን ሸለቆ ላከው። ዮሴፍም ሴኬም ደረሰ።
15እዚያም በየሜዳው ሲባዝን ሳለ አንድ ሰው አገኘውና “ምን እየፈለግህ ነው?” ብሎ ጠየቀው።
16ዮሴፍም “ወንድሞቼን እየፈለግሁ ነው፤ መንጋዎቻቸውን ይዘው ወዴት እንደ ተሰማሩ ልትነግረኝ ትችላለህን?” አለው።
17ሰውየውም “እነርሱ ከዚህ ሄደዋል፤ ‘ወደ ዶታን እንሂድ’ ሲሉ ሰምቼአቼዋለሁ” አለው። ስለዚህ የወንድሞቹን ዱካ ተከትሎ ሄደና በዶታን አገኛቸው።
18እነርሱም በሩቅ አዩት፤ ወደ እነርሱም ከመድረሱ በፊት ሊገድሉት ተማከሩ። 19እርስ በርሳቸውም “እነሆ፥ ያ ሕልም አላሚ መጣ፤ 20ኑ እንግደለውና ከእነዚህ ጒድጓዶች በአንደኛው ውስጥ እንጣለው፤ ከዚህ በኋላ ‘ክፉ አውሬ በላው’ ብለን ማመኻኘት እንችላለን፤ በዚህ ዐይነት የሕልሙን መጨረሻ እናያለን” አሉ።
21ሮቤል ይህንን በሰማ ጊዜ ከእጃቸው ለማዳን በመፈለግ “ተዉ፤ አይሆንም፤ ባንገድለው ይሻላል፤ 22ከምትገድሉት ይልቅ በዚህ በበረሓ ባለው ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት” አላቸው። ሮቤል ይህን ያለው ከእጃቸው አድኖ ወደ አባቱ ሊመልሰው ፈልጎ ነው። 23ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ በደረሰ ጊዜ ጌጠኛ የሆነውን እጀ ጠባቡን አወለቁበት፤ 24ዮሴፍንም ወስደው ውሃ በሌለው ደረቅ ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት።
25ከዚህ በኋላ ምሳ ለመብላት ተቀመጡ፤ በሚመገቡበትም ጊዜ እስማኤላውያን ነጋዴዎችን በሩቅ አዩ፤ እነርሱም በግመሎቻቸው ቅመማ ቅመም፥ በለሳን፥ ከርቤም ጭነው ከገለዓድ ወደ ግብጽ የሚጓዙ ነበሩ።
26በዚህ ጊዜ ይሁዳ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን ገድለን የአሟሟቱን ሁኔታ ብንደብቅ ምን ይጠቅመናል? 27እርሱ የሥጋ ወንድማችን ስለ ሆነ” በእርሱ ላይ ጒዳት ከምናደርስበት ይልቅ ለእነዚህ እስማኤላውያን ነጋዴዎች ብንሸጠው ይሻላል፤ ወንድሞቹም በዚህ ሐሳብ ተስማሙ። 28የምድያም ነጋዴዎች የሆኑ እስማኤላውያን በዚያ በኩል ያልፉ ነበር፤ ስለዚህ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጒድጓድ ጐትተው በማውጣት ለእነዚህ እስማኤላውያን በሃያ ብር ሸጡላቸው፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይዘውት ሄዱ። #ሐ.ሥ. 7፥9።
29ሮቤል ወደ ጒድጓድ መጥቶ ዮሴፍ በዚያ አለመኖሩን ባወቀ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ 30ወደ ወንድሞቹም ሄደና “እነሆ፥ ልጁ እዚያ የለም! እንግዲህ እኔ ወዴት ብሄድ ይሻለኛል?” አለ።
31ከዚህ በኋላ አንድ ፍየል ዐረዱና የዮሴፍን ልብስ በደም ነከሩት። 32ብዙ ኅብር ያለበትንም ልብሱን ወደ አባታቸው ወስደው “እነሆ፥ ይህን አገኘን የልጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እይ” አሉት።
33እርሱም የልጁ ልብስ መሆኑን ተረድቶ “በእርግጥ የእርሱ ልብስ ነው! አንድ ክፉ አውሬ ገድሎታል፤ ልጄን ዮሴፍን አውሬ ቦጫጭቆ በልቶታል!” አለ። 34ከዚህ በኋላ ልብሱን በሐዘን ቀደደ፤ ማቅ በወገቡ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀኖች አለቀሰ። 35ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ሁሉ ሊያጽናኑት ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱ ግን “ለልጄ እያለቀስሁ ወደ ሙታን ዓለም እወርዳለሁ” በማለት መጽናናትን እምቢ አለ። ስለዚህ ስለ ልጁ ማዘኑን ቀጠለ።
36በዚያን ጊዜ የምድያም ሰዎች እስማኤላውያን ዮሴፍን በግብጽ አገር ለጶጢፋር ሸጡት፤ ጶጢፋር ከፈርዖን ባለሥልጣኖች አንዱ የሆነ የዘበኞቹ አለቃ ነበር።
Voafantina amin'izao fotoana izao:
ኦሪት ዘፍጥረት 37: አማ05
Asongadina
Hizara
Dika mitovy
Tianao hovoatahiry amin'ireo fitaovana ampiasainao rehetra ve ireo nasongadina? Hisoratra na Hiditra
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997