ኦሪት ዘፍጥረት 36
36
የዔሳው ዘሮች
(1ዜ.መ. 1፥34-37)
1ኤዶም የተባለው የዔሳው የትውልድ ታሪክ የሚከተለው ነው፤ 2ዔሳው ከነዓናውያን ሴቶችን አገባ፤ እነርሱም የሒታዊው የኤሎን ልጅ ዓዳ፥ የሒዋዊው የጺባዖን ልጅ ዐና የወለዳት ኦሆሊባማን እና፥ #ዘፍ. 26፥34። 3የነባዮት እኅት የነበረችው የእስማኤል ልጅ ባሴማት ናቸው። #ዘፍ. 28፥9። 4ዓዳ ለዔሳው ኤሊፋዝን ወለደችለት፤ ባሴማትም ረዑኤልን ወለደችለት፤ 5ኦሆሊባማም የዑሻን፥ ያዕላምንና ቆሬን ወለደችለት። እነዚህ ሁሉ ለዔሳው በከነዓን ምድር የተወለዱለት ልጆች ናቸው።
6ከዚህ በኋላ ዔሳው ሚስቶቹን ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፥ በቤቱ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ መንጋዎቹንና ሌሎቹንም ከብቶች ሁሉ፥ በከነዓን ሳለ ያፈራውን ንብረት ሁሉ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደ። 7ይህንንም ያደረገበት ምክንያት እርሱና ያዕቆብ ብዙ ንብረት ስለ ነበራቸው፥ የሚሰፍሩበት ምድር ለሁለት ስላልበቃ ነው፤ ሁለቱም ብዙ እንስሶች ስለ ነበሩአቸው አብረው ለመኖር አልቻሉም። 8ስለዚህ ኤዶም የተባለው ዔሳው በተራራማው አገር በኤዶም ተቀመጠ።
9በተራራማው አገር በኤዶም ይኖሩ የነበሩት ኤዶማውያን ቅድመ አያት የነበረው የዔሳው ዘሮች የሚከተሉት ናቸው፤ 10ዔሳው ከሚስቱ ከዓዳ ኤሊፋዝን፥ ከሚስቱ ከባሴማት ረዑኤልን ወለደ።
11የኤልፋዝ ልጆች፦ ቴማን፥ ኦማር፥ ጸፎ፥ ጋዕታምና ቀናዝ ናቸው።
12የዔሳው ልጅ ኤሊፋዝ ቲመናዕ የምትባል ቁባት ነበረችው፤ እርስዋ ለኤሊፋዝ ዐማሌቅን ወለደችለት፤ እነዚህም የዔሳው ሚስት የዓዳ የልጅ ልጆች ናቸው። 13የረዑኤል ልጆች፦ ናሐት፥ ዘራሕ፥ ሻማና ሚዛ ናቸው፤ እነዚህም ዔሳው ባሴማት ከምትባለው ሚስቱ የወለዳቸው የልጅ ልጆች ናቸው።
14የዐና ልጅና የጺባዖን የልጅ ልጅ የነበረችው ኦሆሊባማ ለዔሳው የወለደቻቸው ልጆች፥ የዑሽ፥ ያዕላምና ቆሬ ናቸው።
15የዔሳው መጀመሪያ ልጅ የኤልፋዝ ነገድ አለቆች፦ ቴማን፥ ኦማር፥ ጸፎ፥ ቀናዝ፥ 16ቆሬ፥ ገዕታምና ዐማሌቅ፤ እነዚህ በኤዶም የኤልፋዝ ነገድ አለቆች ሲሆኑ፥ እነርሱም ዔሳው ከሚስቱ ከዓዳ የወለዳቸው ናቸው።
17የዔሳው ልጅ የረዑኤል ነገድ አለቆች፦ ናሐት፥ ዘራሕ፥ ሻማና ሚዛ ሲሆኑ እነዚህ በኤዶም የረዑኤል ነገድ አለቆች ናቸው፤ እነርሱም ዔሳው ከሚስቱ ከባሴማት የወለዳቸው ናቸው።
18ከዔሳው ሚስት ከኦሆሊባማ የተወለዱት የነገድ አለቆች፦ የዑሽ፥ ያዕላምና ቆሬ ናቸው፤ እነዚህ ከዐና ልጅ ከኦሆሊባማ የተወለዱ የዔሳው ትውልድ የነገድ አለቆች ናቸው። 19እነዚህ ሁሉ ኤዶም የተባለው የዔሳው ልጆችና የነገድ አለቆች ናቸው።
የሤዒር ዘሮች
(1ዜ.መ. 1፥38-42)
20በኤዶም ምድር ነዋሪዎች የነበሩት የሤዒር ልጆች የሖራውያን አለቆች፦ ሎጣን፥ ሾባል፥ ጺባዖን፥ ዐና፥ 21ዲሾን፥ ኤጼርና፥ ዲሻን ናቸው።
22ሎጣን የሖሪና የሄማም ጐሣዎች ቅድመ አያት ነበረ። ሎጣን ቲምናዕ የተባለች እኅት ነበረችው።
23የሾባል ልጆችም ዓልዋን፥ ማናሐት፥ ዔባል፥ ስፎና፥ ኦናም ናቸው።
24የጺባዖን ልጆችም አያ እና ዐና ናቸው። ይህም ዐና የአባቱን አህዮች ሲጠብቅ በበረሓ ውስጥ የፍል ውሃ ምንጮችን ያገኘ ሰው ነው።
25የዐናም ልጅ ዲሾን የተባለው ነው፤ ሴት ልጁም ኦሆሊባማ ትባላለች።
26የዲሾን ልጆች ሔምዳን፥ ኤሽባን፥ ይትራንና፥ ከራን ናቸው።
27የኤጼር ልጆች ቢልሃን፥ ዛዕዋንና፥ ዓቃን ናቸው።
28የዲሻን ልጆች ዑፅና አራን ናቸው።
29የሖሪው አለቆች የሚከተሉት ናቸው፤ ሎጣን፥ ሾባል፥ ጺባዖን፥ ዐና፥ 30ዲሾን፥ ኤጼር፥ ዲሻን፤ እነዚህ ሁሉ በኤዶም ምድር አለቆች የሆኑ የሖሪው ዘሮች ናቸው።
የኤዶም ነገሥታት
(1ዜ.መ. 1፥43-54)
31በእስራኤል ንጉሥ መንገሥ ከመጀመሩ በፊት በኤዶም ምድር የነገሡት ነገሥታት የሚከተሉት ናቸው፤
32የበዖር ልጅ ቤላዕ በኤዶም ነገሠ፤ የነገሠባትም ከተማ ዲንሃባ ትባል ነበር።
33ቤላዕ በሞተ ጊዜ የቦጽራ አገር ተወላጅ የዘራሕ ልጅ ዮባብ በእርሱ እግር ተተክቶ ነገሠ።
34ዮባብም በሞተ ጊዜ የቴማን አገር ተወላጅ ሑሻም በእርሱ እግር ተተክቶ ነገሠ።
35ሑሻምም በሞተ ጊዜ የምድያምን ሰዎች በሞአብ ሜዳ ድል የመታው የበዳድ ልጅ ሀዳድ በእርሱ ተተክቶ ነገሠ፤ የነገሠባትም ከተማ ዐዊት ትባል ነበር።
36ሀዳድ በሞተ ጊዜ የማሥሬቃ ተወላጅ ሠምላ በእርሱ እግር ተተክቶ ነገሠ።
37ሠምላ በሞተ ጊዜ በወንዝ አጠገብ ያለችው የረሖቦት ተወላጅ የነበረው ሻኡል በእርሱ ተተክቶ ነገሠ። 38ሻኡል በሞተ ጊዜ የዐክቦር ልጅ በዐል ሐናን በእርሱ እግር ተተክቶ ነገሠ።
39የዐክቦር ልጅ ባዓል ሐናንም በሞተ ጊዜ ሀዳር በእርሱ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ የነገሠባትም ከተማ ፋዑ ትባል ነበር፤ ሚስቱም የሜዛሃብ ልጅ ማጥሬድ የወለደቻት መሄጣብኤል ትባል ነበር።
40የሚከተሉትም የዔሳው ዘር የነገድ አለቆች በየጐሣቸው ስምና በየሚኖሩበት ቦታ ስም ይጠራሉ፤ ቲምናዕ፥ ዐልዋ፥ ዬቴት፥ 41ኦሆሊባማ፥ ኤላ፥ ፊኖን፥ 42ቀናዝ፥ ቴማን፥ ሚብጻር፥ 43ማግዲኤልና ዒራም። በየመኖሪያ ስፍራቸው ስም የሚጠሩት የኤዶም አለቆች እነዚህ ናቸው። ይህም ዔሳው የኤዶማውያን አባት ነው።
Voafantina amin'izao fotoana izao:
ኦሪት ዘፍጥረት 36: አማ05
Asongadina
Hizara
Dika mitovy
Tianao hovoatahiry amin'ireo fitaovana ampiasainao rehetra ve ireo nasongadina? Hisoratra na Hiditra
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997