Logo YouVersion
Icona Cerca

ዘፍጥረት 1

1
የፍጥረት አጀማመር
1በመጀመሪያ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ። 2ምድርም ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች።#1፥2 ወይም ሆነች የምድርን ጥልቅ ስፍራ ሁሉ ጨለማ ውጦት ነበር። የእግዚአብሔርም (ኤሎሂም) መንፈስ በውሆች ላይ ይረብብ ነበር።
3ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) “ብርሃን ይሁን” አለ፤ ብርሃንም ሆነ። 4እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ ብርሃኑን ከጨለማ ለየ። 5እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ብርሃኑን “ቀን”፣ ጨለማውን “ሌሊት” ብሎ ጠራው። መሸ፤ ነጋም፤ የመጀመሪያ ቀን።
6እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ውሃን ከውሃ የሚለይ ጠፈር በውሆች መካከል ይሁን” አለ። 7ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጠፈርን አድርጎ ከጠፈሩ በላይና ከጠፈሩ በታች ያለውን ውሃ ለየ፤ እንዳለውም ሆነ። 8እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጠፈርን “ሰማይ” ብሎ ጠራው። መሸ፤ ነጋም፤ ሁለተኛ ቀን።
9ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ከሰማይ በታች ያለው ውሃ በአንድ ስፍራ ይከማች፤ ደረቁ ምድር ይገለጥ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። 10እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ደረቁን ምድር፣ “የብስ”፣ በአንድነት የተሰበሰበውን ውሃ፣ “ባሕር” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ።
11እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ምድር ዕፀዋትንም፣ እንደየወገናቸው ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና በምድር ላይ ዘር ያዘሉ ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ታብቅል” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። 12ምድር ዕፀዋትን፣ እንደየወገናቸው ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና በውስጣቸው ዘር ያለባቸው ፍሬ የሚያፈሩትን ዛፎች በየወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። 13መሸ፤ ነጋም፤ ሦስተኛ ቀን።
14ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ቀኑን ከሌሊት እንዲለዩ፣ የዓመት ወቅቶች፣ ቀናትና ዓመታት የሚጀምሩበትንም እንዲያመለክቱ፣ 15ለምድር ብርሃን የሚሰጡ ልዩ ልዩ ብርሃናት በሰማይ ይሁኑ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። 16እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ ለምድር ብርሃን ይሰጡ ዘንድ ሁለት ታላላቅ ብርሃናት አደረገ፤ ታላቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፣ ታናሹ ብርሃን በሌሊት እንዲሠለጥን አደረገ። እንዲሁም ከዋክብትን አደረገ። 17ለምድር ብርሃን እንዲሰጡ እነዚህን በሰማይ ጠፈር አኖራቸው። 18ይኸውም በቀንና በሌሊት እንዲሠለጥኑ፣ ብርሃንን ከጨለማ እንዲለዩ ነው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። 19መሸ፤ ነጋም፣ አራተኛ ቀን።
20እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ውሆች ሕይወት ባላቸው በሕያዋን ፍጡራን ይሞሉ፤ ወፎች ከምድር በላይ በሰማይ ጠፈር ይብረሩ” አለ። 21በዚህ መሠረት፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ታላላቅ ፍጡራንን፣ በውሃ ውስጥ የሚርመሰመሱ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ እንደየወገናቸው እንዲሁም ክንፍ ያላቸውን ወፎች ሁሉ እንደየወገናቸው ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። 22እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ብዙ ተባዙ፤ የባሕርንም ውሃ ሙሏት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው። 23መሸ፤ ነጋም፤ አምስተኛ ቀን።
24እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ምድር ሕያዋን ፍጡራንን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንንና የዱር እንስሳትን እያንዳንዱን እንደ ወገኑ ታስገኝ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። 25እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን እንደየወገናቸው፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንን እንደየወገናቸው አደረገ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ።
26እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር#1፥26 ዕብራይስጡም እንደዚሁ ሲሆን ሱርስቱ ግን የዱር እንስሳት ሁሉ ይለዋል። ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር በሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ።
27ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤
በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልክ ፈጠረው፤
ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
28እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው” ብሎ ባረካቸው።
29እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እንዲህ አለ፤ “በምድር ላይ ያሉትን ዘር የሚሰጡ ተክሎችን ሁሉ፣ በፍሬያቸው ውስጥ ዘር ያለባቸውን ዛፎች ሁሉ ምግብ ይሆኑላችሁ ዘንድ ሰጥቻችኋለሁ። 30እንዲሁም ለምድር አራዊት ሁሉ፣ ለሰማይ ወፎች ሁሉ፣ በምድር ላይ ለሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ማንኛውም ለምለም ተክል ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቻለሁ” እንዳለውም ሆነ።
31እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ። መሸ፤ ነጋም፤ ስድስተኛ ቀን።

Attualmente Selezionati:

ዘፍጥረት 1: NASV

Evidenziazioni

Condividi

Copia

None

Vuoi avere le tue evidenziazioni salvate su tutti i tuoi dispositivi?Iscriviti o accedi

Video per ዘፍጥረት 1