የዮሐንስ ወንጌል 12
12
ጌታችንን ሽቱ ስለ ቀባችው ሴት
1ፋሲካ ከሚውልበት ከስድስተኛው ቀን አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ። 2በዚያም ምሳ አደረጉለት፤ ማርታም ታሳልፍላቸው ነበር፤ አብረውት ምሳ ከበሉትም አንዱ አልዓዛር ነበር። 3#ሉቃ. 7፥37-38። ማርያም ግን ዋጋዉ የከበረና የበዛ አንድ ነጥር የጥሩ ናርዶስ ሽቱ ወሰደችና የጌታችን ኢየሱስን እግር ቀባችው፤ በፀጕሯም አሸችው፤ የዚያ ሽቱ መዓዛም ቤቱን መላው። 4ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የነበረ ያሲዘው ዘንድ ያለው የስምዖን ልጅ አስቆሮታዊው ይሁዳ ግን እንዲህ አለ። 5“ለነዳያን ይሰጥ ዘንድ ይህን ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ለምን አልሸጡትም?” 6ይህንም ያለ፥ ድሆች አሳዝነውት አይደለም፤ ሌባ ነበርና፥ ሙዳየ ምጽዋቱንም ሲጠብቅ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ነበርና ስለዚህ ነው እንጂ። 7ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለ፥ “ለምቀበርበት ቀን ትጠብቀው ዘንድ ተዉአት። 8#ዘዳ. 15፥11። ድሆች ግን ዘወትር አብረዋችሁ አሉ፤ ዘወትርም ታገኙአቸዋላችሁ፤ በወደዳችሁም ጊዜ መልካም ታደርጉላቸዋላችሁ፤#“ዘወትርም ታገኙአቸዋላችሁ በወደዳችሁም ጊዜ መልካም ታደርጉላቸዋላችሁ” የሚለው በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ የለም። እኔን ግን ዘወትር የምታገኙኝ አይደለም።”
9ከአይሁድም ብዙ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ በዚያ እንዳለ በዐወቁ ጊዜ ወደ እርሱ መጡ፤ የመጡትም ጌታችን ኢየሱስን ለማየት ብቻ አልነበረም፤ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ለይቶ ያስነሣዉን አልዓዛርንም ያዩ ዘንድ ነበር እንጂ። 10የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ሊገድሉት ተማከሩ። 11ከአይሁድ ብዙዎች ስለ እርሱ እየሄዱ በጌታችን በኢየሱስ ያምኑ ነበርና።
ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መግባቱ
12በማግሥቱም ለበዓል መጥተው የነበሩ ብዙ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመጣ በሰሙ ጊዜ፥ 13#መዝ. 117፥25-26። የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው “ሆሣዕና በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ፥ የእስራኤልም ንጉሥ ቡሩክ ነው” እያሉ ወጥተው ተቀበሉት። 14ጌታችን ኢየሱስም የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርስዋ ላይ ተቀመጠ። 15#ዘካ. 9፥9። “የጽዮን ልጅ ሆይ፥ አትፍሪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ይመጣል” ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ 16ደቀ መዛሙርቱም አስቀድመው ይህን ነገር አላወቁም፤ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያ ጊዜ ይህ ነገር ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ፥ ይህንም እንደ አደረጉለት ትዝ አላቸው። 17ከዚያም አብረውት የነበሩት ሕዝብ አልዓዛርን ከመቃብር እንደ ጠራው፥ ከሙታንም እንደ አስነሣው መሰከሩለት። 18ስለዚህም ነገር ሕዝቡ ሁሉ ሊቀበሉት ወጡ፤ ይህን ተአምራት እንደ አደረገ ሰምተዋልና። 19ፈሪሳውያንም እርስ በርሳቸው፥ “የምታገኙት ምንም ጥቅም እንደሌለ ታያላችሁን? እነሆ፥ ዓለም ሁሉ ተከትሎታል” ተባባሉ።
ለበዓል ስለ መጡ ሰዎች
20ከጽርዕ ሰዎችም ይሰግዱ ዘንድ ለበዓል የወጡ ነበሩ። 21እነርሱም ከገሊላ፥ የቤተ ሳይዳ ሰው ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ሄደው፥ “አቤቱ፥ ጌታ ኢየሱስን ልናየው እንወድዳለን” ብለው ለመኑት። 22ፊልጶስም ሄዶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስም ሄደው ለጌታችን ለኢየሱስ ነገሩት። 23ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁን የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ጊዜው ደረሰ። 24እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በምድር ላይ ካልወደቀችና ካልሞተች ብቻዋን ትኖራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ፍሬን ታፈራለች። 25#ማቴ. 10፥39፤ 16፥25፤ ማር. 8፥35፤ ሉቃ. 9፥24፤ 17፥33። ነፍሱን የሚወዳት ይጥላታል፤ በዚህ ዓለም ነፍሱን የሚጥላትም ለዘለዓለም ሕይወት ይጠብቃታል። 26እኔን የሚያገለግለኝ ካለ ይከተለኝ፤ የሚያገለግለኝ እኔ ባለሁበት በዚያ ይኖራልና፤ እኔን የሚያገለግለኝንም አብ ያከብረዋል።
27“አሁንስ ነፍሴ ታወከች፤ ግን ምን እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚች ሰዓት ነፍሴን አድናት፤ ነገር ግን ስለዚህ ነገር ለዚች ሰዓት ደርሻለሁ። 28አባት ሆይ፥ ልጅህን#በግሪኩ እና በአብዛኛው የግእዝ ዘርዕ “ስምህን” ይላል። አክብረው።” ከሰማይም፥ “አከበርሁህ፤ ደግሞም እንደገና አከብርሃለሁ፤” የሚል ቃል መጣ። 29በዚያ ቆመው ይሰሙ የነበሩ ሕዝብ ግን “ነጐድጓድ ነው” አሉ፤ “መልአክ ተናገረው” ያሉም አሉ። 30ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ይህ ቃል የመጣ ስለ እናንተ ነው እንጂ ስለ እኔ አይደለም። 31አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደረሰ፤ ከእንግዲህስ ወዲህ የዚህን ዓለም ገዥ ወደ ውጭ አስወጥተው ይሰዱታል። 32እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ካልሁ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።” 33ይህንም ያለ በምን ዐይነት ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ነው። 34#መዝ. 109፥4፤ ኢሳ. 9፥7፤ ሕዝ. 37፥25፤ ዳን. 7፥14። ሕዝቡም፥ “እኛስ ክርስቶስ ለዘለዓለም እንዲኖር በኦሪት ሰምተን ነበር፤ እንግዲህ እንዴት አንተ ‘የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ አለው’ ትለናለህ? እንግዲህ ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?” ብለው መለሱለት። 35ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “ ገና ለጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው፤ በጨለማ የሚመላለስ የሚሄድበትን አያውቅምና ጨለማ እንዳያገኛችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ 36የብርሃን ልጆች ትሆኑ ዘንድ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን እመኑ” ጌታችን ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደ፤ ተሰወራቸውም። 37ይህንም ያህል ተአምራት በፊታቸው ሲያደርግ አላመኑበትም። 38#ኢሳ. 53፥1። “አቤቱ፥ ምስክርነታችንን ማን ያምነናል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ?” ያለው የነቢዩ የኢሳይያስ ቃል ይደርስ ዘንድ። 39ስለዚህም ማመን ተሳናቸው፤ ኢሳይያስ ዳግመኛ እንዲህ ብሎአልና። 40#ኢሳ. 6፥10። “በዐይናቸው አይተው፥ በልባቸውም አስተውለው እንዳይመለሱና እንዳልፈውሳቸው ዐይኖቻቸው ታወሩ፤ ልባቸውም ደነደነ።” 41ኢሳይያስ ጌትነቱን አይቶአልና፥ ይህን ተናገረ፤ ስለ እርሱም መሰከረ። 42ከሕዝቡ አለቆችም ያመኑበት ብዙዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ከምኵራብ አስወጥተው እንዳይሰዱአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም። 43ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና።
44ጌታችን ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፥ “በእኔ የሚያምን በላከኝም ነው እንጂ በእኔ ብቻ የሚያምን አይደለም። 45እኔን ያየ የላከኝን አየ። 46በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን እኔ ወደ ዓለም መጣሁ። 47ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀውን እኔ የምፈርድበት አይደለሁም፤ ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድበት አልመጣሁምና። 48የሚክደኝን፥ ቃሌንም የማይቀበለውን ግን የሚፈርድበት አለ፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻዪቱ ቀን ይፈርድበታል። 49የተናገርሁት ከእኔ የሆነ አይደለምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እንድናገር፥ እንዲህም እንድል እርሱ ትእዛዝን ሰጠኝ። 50ትእዛዙም የዘለዓለም ሕይወት እንደ ሆነ አውቃለሁ፤ እኔም የምናገረውን አብ እንዳለኝ እንዲሁ እናገራለሁ።”
Pilihan Saat Ini:
የዮሐንስ ወንጌል 12: አማ2000
Sorotan
Berbagi
Salin
Ingin menyimpan sorotan di semua perangkat Anda? Daftar atau masuk