የሉቃስ ወንጌል 22
22
የካህናት አለቆች ጌታን ለመግደል እንደ ፈለጉ
1 #
ዘፀ. 12፥1-27። ፋሲካም የሚባለው የቂጣ በዓል ቀረበ። 2የካህናት አለቆችና ጻፎችም ሊገድሉት ይሹ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ይፈሩአቸው ነበር።
ይሁዳ ጌታን አሳልፎ ለመስጥት እንደ ተስማማ
3ቍጥሩ ከዐሥራ ሁለቱ በነበረው በአስቆሮቱ ይሁዳ ልብ ሰይጣን አደረ። 4ሄዶም ከካህናት አለቆችና ከታላላቆች ጋር እርሱን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ተነጋገረ። 5ደስ ብሏቸውም ሠላሳ ብር#“ሰላሳ ብር” የሚለው በግሪኩ የለም። ሊሰጡት ተስማሙ። 6እርሱም እሺ አለ፤ ሰው ሳይኖርም እርሱን አሳልፎ ሊሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር።
የፋሲካን በግ ስለ ማዘጋጀት
7የፋሲካን በግ የሚያርዱባት የቂጣ በዓልም ደረሰች። 8ጌታችን ኢየሱስም ጴጥሮስንና ዮሐንስን፥ “ሂዱና የምንበላውን የፋሲካ በግ አዘጋጁልን” አላቸው። 9እነርሱም፥ “ወዴት ልናዘጋጅልህ ትወዳለህ?” አሉት። 10እንዲህም አላቸው፥ “ወደ ከተማ በገባችሁ ጊዜ፥ የውኃ ማድጋ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ ወደሚገባበትም ቤት እርሱን ተከተሉት። 11የዚያን ቤት ጌታ፦ መምህር ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን በግ የምበላበት ቤት ወዴት ነው? ብሎሃል በሉት። 12እርሱም በሰገነት ላይ የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁልን።” 13በሄዱም ጊዜ እንዳላቸው አገኙ፤ የፋሲካውንም በግ አዘጋጁ።
ስለ ምሥጢረ ቍርባን
14ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ በማዕድ ተቀመጠ፤ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱም ከእርሱ ጋር ተቀመጡ። 15እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ከመከራዬ አስቀድሞ ይህን ፋሲካ ከእናንተ ጋር ልበላ እጅግ ወደድሁ። 16ነገር ግን፤ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ እንግዲህ ከእርሱ እንደማልበላ እነግራችኋለሁ” አላቸው። 17ጽዋውንም ተቀብሎ አመሰገነ፤ እንዲህም አለ፥ “ይህን እንኩ ሁላችሁም ተካፈሉት። 18እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ፤#በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን እስክጠጣው ድረስ” ይላል። እንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።” 19ኅብስቱንም አነሣ፤ አመስገነ፤ ፈትቶም ሰጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “ስለ እናንተ ቤዛ ሆኖ የሚሰጥ ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህንም ለመታሰቢያዬ አድርጉት፤” 20#ኤር. 31፥31-34። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋዉን አንሥቶ እንዲህ አላቸው፥ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈስሰው ደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።
ስለሚያሲዘው ሰው የተሰጠ ምልክት
21 #
መዝ. 40፥9። “ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ እነሆ፥ በማዕድ ከእኔ ጋር ነው። 22የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በእጁ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት።” 23ደቀ መዛሙርቱም ከእነርሱ ይህን የሚያደርግ ማን እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።
ስለ ትሕትና
24 #
ማቴ. 18፥1፤ ማር. 9፥34፤ ሉቃ. 9፥46። ከዚህም በኋላ ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። 25#ማቴ. 20፥25-27፤ ማር. 10፥42-44። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “አሕዛብን ንጉሦቻቸው ይገዙአቸዋል፤ በላያቸውም ሥልጣን ያላቸው ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። 26#ማቴ. 23፥11፤ ማር. 9፥35። ለእናንተ ግን እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቁ እንደ ታናሽ ይሁናችሁ፤ አለቃውም እንደ አገልጋይ ይሁን። 27#ዮሐ. 13፥12-15። የሚበልጥ ማንኛው ነው? በማዕድ ላይ የተቀመጠው ነው? ወይስ የሚላላከው? በማዕድ ላይ የተቀመጠው አይደለምን? እነሆ፥ እኔ በመካከላችሁ እንደ አገልጋይ ነኝ። 28ነገር ግን ስለ እኔ የታገሣችሁ እናንተ በመከራዬ ከእኔ ጋር ናችሁ። 29አባቴ ለእኔ እንደ ሰጠኝ፥ እኔም ለእናንተ መንግሥትን አዘጋጅላችኋለሁ፤ 30#ማቴ. 19፥28። በመንግሥቴ በማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በወንበሮችም ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ትፈርዱ ዘንድ።”
ሃይማኖትን ስለ ማጽናት
31ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለ፥ “ስምዖን፥ ስምዖን ሆይ፥ ሰይጣን እንደ አጃ ሊያበጥራችሁ አሁን ልመናን ለመነ። 32እኔ ግን ሃይማኖታችሁ እንዳይደክም ስለ እናንተ ጸለይሁ፤ አንተም ተመልሰህ ወንድሞችህን አጽናቸው።” 33እርሱም፥ “አቤቱ፥ እኔ ለመታሰርም ቢሆን፥ ለሞትም ቢሆን እንኳ ከአንተ ጋራ ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ” አለው። 34እርሱ ግን፥ “ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ እንደማታውቀኝ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። 35#ማቴ. 10፥9-10፤ ማር. 6፥8-9፤ ሉቃ. 9፥3፤ 10፥4። ደግሞም፥ “ያለ ስልቻ፥ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ በውኑ የተቸገራችሁት ነገር ነበርን?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “የለም” አሉት። 36እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “አሁን ግን ኮሮጆ ያለው ኮሮጆውን ይያዝ፤ ከረጢትም ያለው እንዲሁ ያድርግ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። 37#ኢሳ. 53፥12። እላችኋለሁ፥ ከኃጥኣን ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ይደርሳል፤ ስለ እኔ የተጻፈውም ሁሉ ይፈጸማል።” 38እነርሱም፥ “አቤቱ፥ እነሆ፥ እዚህ በእኛ ዘንድ ሁለት ሰይፎች አሉ” አሉት፤ እርሱም፥ “እንግዲያስ ይበቃችኋል” አላቸው።
በደብረ ዘይት ስለ መጸለዩ
39ወጥቶም እንዳስለመደው ይጸልይ ዘንድ#“ይጸልይ ዘንድ” የሚለው በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ የለም። ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። 40ከዚያም ደርሶ፥ “ወደ መከራ እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። 41የድንጋይ ውርወራ ያህልም ከእነርሱ ፈቀቅ ብሎ እየሰገደ ጸለየ። 42እንዲህም አለ፥ “አባት ሆይ፥ ብትፈቅድስ ይህን ጽዋ ከእኔ አሳልፈው፤ ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” 43የሚያበረታታው የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ታየው። 44ፈራ፤ መላልሶም ጸለየ፤ ላቡም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ሆነ። 45ከሚጸልይበትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄደ፤ ከኀዘንም የተነሣ ተኝተው አገኛቸው። 46“ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ” አላቸው።
በአይሁድ እጅ ስለ መግባቱ
47ይህንም ሲነግራቸው ሕዝቡ ደረሱ፤ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ አንዱ ይሁዳም ይመራቸው ነበር፤ ወደ ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ ሳመው፤ የሰጣቸውም ምልክት ይህ ነበር፤ “የምስመው እርሱ ነውና እርሱን አጽንታችሁ ያዙት”#“የምስመው እርሱ ነውና እርሱን አጽንታችሁ ያዙት” የሚለው በግሪኩና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ የለም። አላቸው። 48ጌታችን ኢየሱስም ይሁዳን፥ “በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጠዋለህን?” አለው። 49አብረውት የነበሩትም የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ጌታችን ኢየሱስን፥ “አቤቱ፥ በሰይፍ ልንመታቸው ትፈቅዳለህን?” አሉት። 50ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መታው፤ ቀኝ ጆሮውንም ቈረጠው። 51ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ይህንስ ተው” አለ፤ ወዲያውም ጆሮውን ዳስሶ አዳነው። 52ጌታችን ኢየሱስም ሊይዙት ወደ እርሱ የመጡትን የካህናት አለቆችን፥ የቤተ መቅደስ ሹሞችንና ሽማግሌዎችን እንዲህ አላቸው፥ “ሌባን እንደምትይዙ በሰይፍና በጎመድ ልትይዙኝ መጣችሁን? 53#ሉቃ. 19፥47፤ 21፥37። ዘወትርም ከእናንተ ጋር በቤተ መቅደስ ስኖር እጃችሁን እንኳ አልዘረጋችሁብኝም፤ ነገር ግን ጊዜያችሁ ይህ ነው፤ የጨለማው አበጋዝም ሥልጣኑ ይህ ነው።”
ስለ ጴጥሮስ ክሕደት
54ይዘውም ወደ ሊቀ ካህናቱ ቤት ወሰዱት፤ ጴጥሮስም ከሩቅ ይከተለው ነበር። 55በግቢውም ውስጥ እሳት አንድደው ተቀመጡ፤ ጴጥሮስም አብሮአቸው በመካከላቸው ተቀመጠ። 56በእሳቱም ብርሃን በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት ብላቴና አየችው፤ እርሱ መሆኑንም ለየችውና፥ “ይህም ከእርሱ ጋር ነበር” አለች። 57እርሱ ግን፥ “ሴትዮ! የምትዪውን አላውቅም” ብሎ ካደ። 58ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላ ሰው አየውና፥ “አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ” አለው፤ ጴጥሮስ ግን፥ “አንተ ሰው! እኔ አይደለሁም” አለው። 59አንዲት ሰዓት ያህልም ቈይቶ አንድ ሌላ ሰው፥ “ይህም በእውነት ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ሰውየውም የገሊላ ሰው ነው” ብሎ አስጨነቀው። 60ጴጥሮስ ግን፥ “አንተ ሰው! የምትለውን አላውቅም” አለው፤ እርሱም ይህን ሲናገር ያንጊዜ ዶሮ ጮኸ። 61ጌታችን ኢየሱስም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን አየው፤ ጴጥሮስም፥ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለውን የጌታችንን ቃል ዐሰበ። 62ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ መራራ ልቅሶን አለቀሰ።
አይሁድ በጌታችን በኢየሱስ ላይ ስለ መዘባበታቸው
63ጌታችን ኢየሱስን ይዘውት የነበሩት ሰዎችም ይዘባበቱበትና ይደበድቡት ነበር። 64ሸፍነውም ፊቱን በጥፊ ይመቱት ነበር፤ “ፊትህን በጥፊ የመታህ ማነው? ንገረን” እያሉም ይጠይቁት ነበር። 65ሌላም ብዙ ነገር እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር።
በአደባባይ ስለ መቆሙ
66በነጋም ጊዜ፥ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱት። 67“አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ በግልጥ ንገረን” አሉት፤ እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ብነግራችሁም አታምኑኝም። 68ብጠይቃችሁም አትመልሱልኝም፤ ወይም አትተዉኝም። 69ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኀይል ቀኝ ይቀመጣል።” 70ሁሉም፥ “እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት፤ እርሱም፥ “እኔ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ” አላቸው። 71እነርሱም፥ “ስለ እርሱ ምን ምስክር እንሻለን? እኛ ራሳችን ሲናገር ሰምተናል” አሉ።
Trenutno odabrano:
የሉቃስ ወንጌል 22: አማ2000
Istaknuto
Podijeli
Kopiraj
Želiš li svoje istaknute stihove spremiti na sve svoje uređaje? Prijavi se ili registriraj