YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 13

13
የዘሪው ምሳሌ
(ማር. 4፥1-9ሉቃ. 8፥4-8)
1በዚያኑ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ 2ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው በመሰብሰባቸው በጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ፥ በባሕር ዳር ቆመው ነበር። #ሉቃ. 5፥1-3። 3ከዚያም በኋላ ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ እያለ ይነግራቸው ጀመር፦ “እነሆ! አንድ ገበሬ ለመዝራት ወጣ። 4ሲዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። 5ሌላው ዘር ብዙ ዐፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ መሬቱም ብዙ ዐፈር ስለሌለበት ጥልቀት አልነበረውም፤ ስለዚህ ዘሩ ወዲያውኑ በቀለ። 6ይሁን እንጂ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፤ ሥር ስላልነበረውም ደረቀ። 7ሌላውም ዘር በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል ወደቀ፤ እሾኻማውም ቊጥቋጦ አደገና የዘሩን ቡቃያ አንቆ አስቀረው። 8ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለና ብዙ ፍሬ አፈራ፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። 9ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”
ኢየሱስ ስለምን በምሳሌ ይናገር እንደ ነበረ
(ማር. 4፥10-12ሉቃ. 8፥9-10)
10ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ስለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። 11እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። 12ላለው ሰው የበለጠ ይሰጠዋል፤ ይበዛለታልም፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። #ማቴ. 25፥29፤ ማር. 4፥25፤ ሉቃ. 8፥18፤ 19፥26። 13እያዩ እንደማያዩ፥ እየሰሙ እንደማይሰሙ ወይም እንደማያስተውሉ ስለ ሆኑ እነሆ፥ እኔ በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። 14ስለዚህ በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው በእነርሱ ላይ ይፈጸማል፦
‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤
ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አታደርጉም።
15የእዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፤
ጆሮአቸው ተደፍኖአል፤ ዐይናቸውም ተጨፍነዋል፤
እንዲህስ ባይሆን ኖሮ፥ በዐይናቸው ተመልክተው፥
በጆሮአቸውም ሰምተው፥
በልባቸውም አስተውለው፥
ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኳቸው ነበር።’ #ኢሳ. 6፥9-10።
16“የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ የተባረኩ ናቸው። 17በእውነት እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አላዩም፤ እናንተ የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አልሰሙም። #ሉቃ. 10፥23-24።
የዘሪው ምሳሌ ትርጒም
(ማር. 4፥13-20ሉቃ. 8፥11-15)
18“እንግዲህ እናንተ የዘሪው ምሳሌ ምን እንደ ሆነ ስሙ፤ 19በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ የማያስተውለውን ሰው ነው፤ ወዲያውኑ ሰይጣን መጥቶ በልቡ የተዘራውን ቃል ይወስድበታል፤ 20በጭንጫማ መሬት ላይ የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ነው። 21ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በልቡ ውስጥ ሥር አልሰደደም፤ ስለዚህ በቃሉ ምክንያት አንዳች ችግር ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ቶሎ ይሰናከላል። 22በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ለጊዜው የሚሰማውን ሰው ነው፤ ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ሐሳብና የሀብት ፍቅር ወደ ልቡ ገብቶ ቃሉን ስለሚያንቀው ያለ ፍሬ ይቀራል። 23በመልካም መሬት ላይ የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ሰምቶ በማስተዋል የሚቀበለውን ሰው ነው፤ እርሱ ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱ ሠላሳ ፍሬ ይሰጣል።”
የእንክርዳድ ምሳሌ
24እንዲሁም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻው መልካም ዘር የዘራውን ሰው ትመስላለች፤ 25ነገር ግን ሰው ሁሉ ከተኛ በኋላ ጠላት መጣና በስንዴው ውስጥ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። 26ስንዴው አድጎ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም በዚያኑ ወቅት ታየ። 27ስለዚህ የእርሻው ባለቤት አገልጋዮች ወደ እርሱ ቀርበው ‘ጌታ ሆይ፥ በእርሻህ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ፥ እንክርዳዱ ከወዴት መጣ?’ አሉት። 28እርሱም ‘ይህን ያደረገ ጠላት ነው’ አላቸው። አገልጋዮቹም ‘ታዲያ ሄደን እንክርዳዱን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?’ አሉት። 29እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው ‘አይሆንም እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውን አብራችሁ ትነቅላላችሁ። 30ስለዚህ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ ድረስ ስንዴውም እንክርዳዱም አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜ ዐጫጆችን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳት እንዲቃጠልም በየነዶው እሰሩ፤ ስንዴውን ግን ሰብስቡና በጐተራዬ ክተቱ’ እላቸዋለሁ።”
የሰናፍጭ ዘር ምሳሌ
(ማር. 4፥30-32ሉቃ. 13፥18-19)
31ኢየሱስ ሌላ ምሳሌም እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማይ አንድ ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች። 32እርስዋ ከዘር ሁሉ ያነሰች ናት ባደገች ጊዜ ግን፥ ከአትክልቶች ሁሉ ትበልጣለች፤ ዛፍም ትሆናለች፤ ወፎችም መጥተው በቅርንጫፎችዋ ላይ ጎጆአቸውን ሠርተው ይሰፍሩባታል።”
የእርሾው ምሳሌ
(ሉቃ. 13፥20-21)
33ደግሞም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማይ አንዲት ሴት ወስዳ ከሦስት መስፈሪያ ዱቄት ጋር የለወሰችውን እርሾ ትመስላለች፤ እርሾውም ሊጡን ሁሉ እንዲቦካ አደረገው።”
ኢየሱስ ለምን በምሳሌዎች እንዳስተማረ
(ማር. 4፥33-34)
34ኢየሱስ ይህን ሁሉ ነገር በምሳሌ ለሕዝቡ ተናገረ፤ ያለ ምሳሌም ምንም ነገር አልተናገራቸውም። 35ይህም የሆነበት ምክንያት በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው እንዲፈጸም ነው፦
“ንግግሬን በምሳሌ እገልጣለሁ፤
ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውን እናገራለሁ።” #መዝ. 78፥2።
ኢየሱስ የእንክርዳዱን ምሳሌ እንዳስረዳ
36ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሕዝቡን አሰናብቶ ወደ ቤት ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፥ “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ትርጒም አስረዳን” አሉት።
37ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ 38እርሻው ይህ ዓለም ነው፤ መልካሙ ዘር የእግዚአብሔር መንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ የሰይጣን ልጆች ናቸው። 39እንክርዳዱን የዘራው ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩ የዓለም መጨረሻ ነው፤ ዐጫጆቹ መላእክት ናቸው። 40ልክ እንክርዳዱ ተነቅሎና በየነዶው ታስሮ እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። 41በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም የኃጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ከእርሱ መንግሥት ሰብስበው ያወጣሉ፤ 42ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። 43ጻድቃን ግን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”
የተሸሸገ ሀብት ምሳሌ
44ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻ ውስጥ የተሸሸገውን ሀብት ትመስላለች። አንድ ሰው ይህን ሀብት ባገኘው ጊዜ መልሶ ደበቀው፤ ከደስታውም ብዛት የተነሣ ሄደና ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛ።”
የዕንቊ ምሳሌ
45እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ደግሞ መንግሥተ ሰማይ ጥሩ ዕንቊ ለመግዛት የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች፤ 46ነጋዴውም እጅግ ክቡር የሆነ ዕንቊ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያንን ዕንቊ ገዛ።”
የመረብ ምሳሌ
47ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እንዲሁም መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር የተጣለች መረብን ትመስላለች፤ እርስዋ በየዐይነቱ ዓሣ የምትሰበስብ ናት፤ 48በሞላች ጊዜ ዓሣ አጥማጆቹ ወደ ባሕሩ ዳር ጐትተው ያወጡአታል፤ ተቀምጠውም መልካም መልካሙን መርጠው በዕቃ ያስቀምጣሉ፤ መጥፎ መጥፎውን ግን ወዲያ ይጥላሉ። 49በዓለም መጨረሻም እንዲህ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን ይለዩአቸዋል። 50ክፉዎችን ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”
51ደግሞም ኢየሱስ፦ “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው።
እነርሱም “አዎን ጌታ ሆይ!” አሉ። 52እርሱም “እንግዲያውስ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ጠንቅቆ የሚያውቅ የሕግ መምህር፦ ከዕቃ ግምጃ ቤቱ አዲስ የሆነውንና አሮጌ የሆነውን ዕቃ የሚያመጣ የንብረት ባለቤትን ይመስላል” ሲል መለሰላቸው።
ኢየሱስ በናዝሬት የደረሰበት ተቃውሞ
(ማር. 6፥1-6ሉቃ. 4፥16-30)
53ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ተናግሮ ካበቃ በኋላ፥ ከዚያ ስፍራ ሄደ። 54ወደ አገሩ ወደ ናዝሬት ከተማ መጥቶ በምኲራቦቻቸው ሕዝብን ያስተምር ነበር፤ የሰሙትም ሁሉ በመደነቅ እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ይህ ሰው ይህን ጥበብና ይህን ድንቅ ሥራ ከወዴት አመጣው? 55ይህ የአናጢው ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም የምትባል አይደለችምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፥ ዮሴፍ፥ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉምን? 56እኅቶቹስ ሁሉ ከእኛ ጋር አይደሉምን? ታዲያ፥ ይህ ሰው ይህን ሁሉ ጥበብ ከየት አገኘው?” 57በዚህም ምክንያት ተሰናክለውበት ሳይቀበሉት ቀሩ። ኢየሱስ ግን፦ “ነቢይ የማይከበረው በሀገሩና በገዛ ቤቱ ብቻ ነው” አላቸው። #ዮሐ. 4፥44። 58ባለማመናቸውም ኢየሱስ በዚያ ብዙ ተአምር አላደረገም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in