YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 12

12
ስለ ሰንበት የቀረበ ጥያቄ
(ማር. 2፥23-28ሉቃ. 6፥1-5)
1በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በስንዴ እርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ርቦአቸው ስለ ነበረ የስንዴ እሸት እየቀጠፉ ይበሉ ጀመር። #ዘዳ. 23፥25። 2ፈሪሳውያን ይህን አይተው ኢየሱስን “ተመልከት! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ!” አሉት። 3ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? #1ሳሙ. 21፥1-6። 4እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ከካህናት በስተቀር እርሱም ሆነ አብረውት የነበሩት ሰዎች ሊበሉት ያልተፈቀደውን፥ የተቀደሰ ኅብስት በላ። #ዘሌ. 24፥9። 5ደግሞስ ካህናት በሰንበት ቀን በቤተ መቅደስ ሰንበትን ሲጥሱ በደል ሆኖ እንደማይቈጠርባቸው በሙሴ አማካይነት በተሰጠው ሕግ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? #ዘኍ. 28፥9-10። 6ነገር ግን ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ እነሆ፥ እዚህ አለ እላችኋለሁ። 7ደግሞም ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ምን እንደ ሆነ ብታስተውሉ ኖሮ በደል በሌለባቸው ሰዎች ላይ ባልፈረዳችሁም ነበር። #ማቴ. 9፥13፤ ሆሴዕ 6፥6። 8እንዲያውም የሰው ልጅ የሰንበትም ጌታ ነው።”
ኢየሱስ እጀ ሽባውን ሰው አዳነ
(ማር. 3፥1-6ሉቃ. 6፥6-11)
9ኢየሱስ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ወደ ምኲራባቸው ገባ፤ 10በዚያም አንድ እጀ ሽባ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስን የሚከሱበትን ምክንያት የፈለጉ አንዳንድ ሰዎች “በሰንበት ቀን በሽተኛን መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ሲሉ ጠየቁት። 11ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው፥ በጉ በሰንበት ቀን በጒድጓድ ውስጥ ቢወድቅበት ስቦ የማያወጣው ማነው? #ሉቃ. 14፥5። 12ታዲያ፥ ከበግ ይልቅ ሰው እንዴት አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት ቀን መልካም ነገር ማድረግ የተፈቀደ ነው።” 13ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እጀ ሽባውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም በዘረጋው ጊዜ እጁ ድኖ ልክ እንደ ደኅነኛው እጅ ሆነለት። 14ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጥተው ኢየሱስን እንዴት አድርገው እንደሚገድሉት ተማከሩ።
የእግዚአብሔር ምርጥ አገልጋይ
15ኢየሱስ ግን ሤራቸውን ዐውቆ ከዚያ ቦታ ገለል አለ፤ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ሄዱ፤ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሳቸው። 16ሰዎቹን ግን ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ 17ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው።
18“እነሆ! የመረጥኩት አገልጋዬ ይህ ነው!
እርሱ እኔ የምወደውና የምደሰትበት ነው፤
መንፈሴን በእርሱ ላይ አደርጋለሁ፤
እርሱም ቅን ፍርድን ለሕዝቦች ያውጃል።
19እርሱ አይከራከርም ወይም አይጮኽም፤
በመንገዶችም ላይ ድምፁን የሚሰማ የለም።
20የተቀጠቀጠ ሸንበቆ እንኳ አይሰብርም፤
የሚጤሰውንም የጥዋፍ ክር አያጠፋም፤
ይህንንም የሚያደርገው፥ ቅን ፍርድ
ድል እስኪነሣ ድረስ ነው።
21አሕዛብ በእርሱ ተስፋ ያደርጋሉ።” #ኢሳ. 42፥1-4።
ኢየሱስና ብዔልዜቡል
(ማር. 3፥20-30ሉቃ. 11፥14-23)
22ከዚህ በኋላ ሰዎች አንድ ጋኔን ያደረበትን ዕውርና ድዳ ሰው ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም ፈወሰው፤ ሰውየውም መናገርና ማየት ቻለ። 23ሕዝቡም ሁሉ ተገርመው፥ “ይህ የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ።
24ፈሪሳውያን ግን ይህን በሰሙ ጊዜ “እርሱ ‘ብዔልዜቡል’ በተባለው በአጋንንት አለቃ አማካይነት ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም” አሉ። #ማቴ. 9፥34፤ 10፥25።
25ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ መንግሥት ተከፋፍሎ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ከሆነ፥ ያ መንግሥት ይወድቃል። እንዲሁም አንድ ከተማ ወይም አንድ ቤተሰብ እርስ በርሱ ከተለያየ ጸንቶ መኖር አይችልም። 26ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ እርስ በርሱ ተለያየ ማለት ነው፤ ታዲያ፥ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊኖር ይችላል! 27ደግሞ እኔ አጋንንትን የማስወጣቸው በብዔልዜቡል ከሆነ፥ ልጆቻችሁስ በምን ያስወጡአቸዋል? ስለዚህ ልጆቻችሁ በእናንተ ላይ ይፈርዱባችኋል። 28እኔ አጋንንትን የማስወጣ በእግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ ግን እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት በእናንተ ላይ መጥታለች ማለት ነው። 29ደግሞስ አንድ ሰው አስቀድሞ ኀይለኛውን ሳያስር ወደ ኀይለኛው ቤት ገብቶ ንብረቱን መዝረፍ እንዴት ይችላል? ኀይለኛውን ካሰረው በኋላ ግን በእርግጥ ንብረቱን ሊዘርፍ ይችላል። 30ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ተቃዋሚዬ ነው፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ይበትናል። #ማር. 9፥40። 31ስለዚህ ሰው የሚያደርገው ማናቸውም ኃጢአት ወይም የስድብ ቃል ሁሉ ይቅር ይባልለታል እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሰው ግን በደሉ ይቅር አይባልለትም። 32በሰው ልጅ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ በደሉ ይቅር ይባልለታል። በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ ግን በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም በደሉ ይቅር አይባልለትም። #ሉቃ. 12፥10።
መልካም ዛፍ በፍሬው የሚታወቅ ስለ መሆኑ
(ሉቃ. 6፥43-45)
33“ዛፍ ሁሉ በፍሬው ስለሚታወቅ መልካም ዛፍ ይኑራችሁ፤ ፍሬውም መልካም ይሆናል፤ ዛፉ መጥፎ ከሆነ ግን ፍሬውም መጥፎ ይሆናል። #ማቴ. 7፥20፤ ሉቃ. 6፥44። 34እናንተ የእባብ ልጆች! ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ነገር መናገር እንዴት ትችላላችሁ? ሰው በአፉ የሚናገረው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን ነው። #ማቴ. 3፥7፤ 23፥33፤ 15፥18፤ ሉቃ. 3፥7፤ 6፥45።
35“መልካም ሰው ከመልካም መዝገቡ፥ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገቡ ክፉ ነገርን ያወጣል። 36በእውነት እላችኋለሁ፤ ሰዎች በግዴለሽነት በሚናገሩት በያንዳንዱ ቃል በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል። 37ከቃልህ የተነሣ ይፈረድልሃል፤ ከቃልህም የተነሣ ይፈረድብሃል።”
ተአምራት ለማየት የቀረበ ጥያቄ
(ማር. 8፥11-12ሉቃ. 11፥29-32)
38በዚያን ጊዜ አንዳንድ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ! አንተ ተአምር ስታደርግ ማየት እንፈልጋለን!” አሉት። #ማቴ. 16፥1፤ ማር. 8፥11፤ ሉቃ. 11፥16። 39እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ክፉና የማያምን ትውልድ ተአምር ለማየት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ተአምር በቀር ሌላ ተአምር አይሰጠውም። #ማቴ. 16፥4፤ ማር. 8፥12። 40ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንዳሳለፈ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በመቃብር ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ያሳልፋል። #ዮናስ 1፥17። 41የነነዌ ከተማ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ዘመን ትውልድ ጋር ተነሥተው በእርሱ ላይ ይፈርዱበታል፤ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት በሰሙ ጊዜ በኃጢአታቸው ተጸጽተው ንስሓ ገብተዋልና። አሁን ግን ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። #ዮናስ 3፥5። 42የደቡብ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ ስለ መጣች በፍርድ ቀን ከዚህ ዘመን ትውልድ ጋር ተነሥታ በእርሱ ላይ ትፈርድበታለች፤ አሁን ግን ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።” #1ነገ. 10፥1-10፤ 2ዜ.መ. 9፥1-12።
የርኩስ መንፈስ በሰው ውስጥ ተመልሶ መግባት
(ሉቃ. 11፥24-26)
43ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ርኩስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ የሚያርፍበት ቦታ በመፈለግ ውሃ በሌለበት በደረቅ ቦታ ይዞራል። ነገር ግን አያገኝም፤ 44ስለዚህ ‘ወደ ወጣሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል። ተመልሶም ሲመጣ፥ ቤቱ ባዶ ሆኖ፥ ጸድቶ፥ ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። 45ከዚህ በኋላ፥ ርኩሱ መንፈስ ይሄድና ከእርሱ ይብስ የከፉትን ሌሎች ሰባት አጋንንት ይዞ ይመጣል። እነርሱም ቀድሞ የጋኔኑ ቤት ወደ ነበረው ሰው ልብ ገብተው አብረው በዚያ ይኖራሉ። ስለዚህ የዚያ ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከመጀመሪያው ይልቅ የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድ ላይ የሚሆነው ይህንኑ የመሰለ ነገር ነው።”
የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ
(ማር. 3፥31-35ሉቃ. 8፥19-21)
46ኢየሱስ ለሕዝቡ ገና ሲናገር ሳለ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። [ 47እዚያ ከነበሩት ሰዎች አንዱ ኢየሱስን፥ “እነሆ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጪ ቆመዋል” አለው።] #12፥47 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች ቊጥር 47 የላቸውም።
48ኢየሱስ ግን “እናቴ ማናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰ። 49ከዚህ በኋላ እጁን ዘርግቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፦ “እናቴና ወንድሞቼ እነሆ፥ እነዚህ ናቸው፤ 50በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም ሁሉ፥ ወንድሜም፥ እኅቴም፥ እናቴም እርሱ ነው።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in