የሉቃስ ወንጌል 18

18
ድኻዋ መበለትና ዐመፀኛው ዳኛ
1ከዚህ በኋላ፥ ኢየሱስ ሳይታክቱ ዘወትር መጸለይ እንደሚገባቸው ለማስተማር ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ 2“በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ፥ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበረ። 3አንዲት መበለትም በዚያች ከተማ ትኖር ነበር፤ እርስዋ ወደ ዳኛው እየመጣች ‘ከባላጋራዬ ጋር ስላለኝ ክርክር ፍርድ ስጠኝ!’ ትለው ነበር። 4እርሱም ፍርድ ሳይሰጣት ብዙ ጊዜ ቈየ፤ በኋላ ግን እንዲህ ሲል አሰበ፤ ‘ምንም እንኳ እግዚአብሔርን ባልፈራ፥ ሰውንም ባላፍር፥ 5ይህች መበለት ስለ ነዘነዘችኝ እፈርድላታለሁ፤ አለበለዚያ ግን ዘወትር እየተመላለሰች ታሰለቸኛለች።’ ”
6ቀጥሎም ጌታ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ግፈኛው ዳኛ የተናገረውን አስተውሉ፤ 7እግዚአብሔር ታዲያ፥ ሌት ተቀን እየጮኹ ለሚለምኑት ሕዝቦቹ አይፈርድላቸውምን? ችላ በማለትስ ርዳታውን ያዘገይባቸዋልን? 8ሳይዘገይ በፍጥነት ይፈርድላቸዋል እላችኋለሁ። ነገር ግን የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆን?”
የትዕቢተኛው ፈሪሳዊና የትሑቱ ቀራጭ ምሳሌ
9ቀጥሎም ኢየሱስ ጻድቃን ነን እያሉ ለሚመኩና ሌሎችንም ለሚንቁ ሰዎች፥ ይህን ምሳሌ ተናገረ፤ 10“ሁለት ሰዎች ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፤ አንዱ ፈሪሳዊ ሲሆን ሌላው ቀራጭ ነበር።
11“ፈሪሳዊው ቆሞ እንዲህ ሲል በልቡ ጸለየ፤ ‘እግዚአብሔር ሆይ! እኔ እንደ ሌሎች ሰዎች ቀማኛ፥ ግፈኛ አመንዝራ ስላልሆንኩ አመሰግንሃለሁ፤ ይልቁንም እንደዚህ እንደ ቀራጭ ስላልሆንኩ አመሰግንሃለሁ። 12እኔ በሳምንት ሁለት ቀን እጾማለሁ፤ ከማገኘው ሁሉ ዐሥራት እያወጣሁ እሰጣለሁ።’
13“ቀራጩ ግን በሩቅ ቆመና፥ ቀና ብሎ ወደ ሰማይ ለማየት እንኳ አልደፈረም፤ ነገር ግን በእጁ ደረቱን እየመታ፥ ‘አምላክ ሆይ! እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ!’ ይል ነበር። 14ጽድቅን አግኝቶ ወደ ቤቱ የተመለሰው ይህ ቀራጭ ነው እንጂ ፈሪሳዊው አይደለም እላችኋለሁ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይላል።” #ማቴ. 23፥12፤ ሉቃ. 14፥11።
ኢየሱስ ሕፃናትን እንደ ባረከ
(ማቴ. 19፥13-15ማር. 10፥13-16)
15ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባዩ ጊዜ ሰዎቹን ተቈጡአቸው። 16ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት እንደእነዚህ ላሉት ስለ ሆነች ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሉአቸው። 17በእውነት እላችኋለሁ! የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን ያልተቀበላት ሰው አይገባባትም።”
የምድር ሀብትና የሰማይ መንግሥት
(ማቴ. 19፥16-30ማር. 10፥17-31)
18ከአይሁድ አለቆች አንዱ ኢየሱስን፥ “ቸር መምህር ሆይ፥ የዘለዓለም ሕይወትን ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባኛል?” ብሎ ጠየቀው።
19ኢየሱስም “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ቸር የለም። 20ትእዛዞችን ታውቃለህ፤ እነርሱም ‘አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህን አክብር’ የተባሉት ናቸው።” #ዘፀ. 20፥12-16፤ ዘዳ. 5፥16-20።
21ሰውየውም “እነዚህን ትእዛዞች ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ” አለው።
22ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ ሰውየውን፥ “እንግዲያውስ ገና አንድ ነገር ማድረግ ይቀርሃል፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ገንዘቡን ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ የተከማቸ ሀብት ታገኛለህ፤ ከዚያም በኋላ መጥተህ ተከተለኝ” አለው። 23ሰውየው ግን በጣም ሀብታም ስለ ነበረ፥ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ። 24ኢየሱስም ሰውየው እንዳዘነ አይቶ፥ እንዲህ አለ፤ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው! 25ሀብታም ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ፥ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል።”
26ይህን የሰሙ ሰዎች፦ “ታዲያ በዚህ ሁኔታ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ።
27ኢየሱስ ግን፥ “በሰው ዘንድ የማይቻል ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” አለ።
28ጴጥሮስም “እነሆ፥ እኛ ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሃል” አለው።
29ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ብሎ ቤቱን ወይም ሚስቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም ወላጆቹን ወይም ልጆቹን የሚተው ሰው፥ 30አሁን በዚህ ዓለም በብዙ እጥፍ ይቀበላል፤ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለምን ሕይወት ያገኛል።”
ኢየሱስ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ለሦስተኛ ጊዜ መናገሩ
(ማቴ. 20፥17-19ማር. 10፥32-34)
31ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ አቅርቦ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ! ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳችን ነው፤ ስለ ሰው ልጅ በነቢያት የተጻፈው ሁሉ በዚያ ይፈጸማል። 32እርሱ ለአሕዛብ ተላልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ያፌዙበታል፤ ይሰድቡታል፤ ይተፉበታል። 33ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፤ ነገር ግን በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣል።”
34ደቀ መዛሙርቱ ግን ከዚህ ሁሉ ነገር አንዱንም አልተረዱም፤ የንግግሩም ምሥጢር ተሰውሮባቸው ስለ ነበር ምን ማለቱ እንደ ሆነ አላወቁም።
ኢየሱስ በኢያሪኮ አንድ ዐይነ ስውር መፈወሱ
(ማቴ. 20፥29-34ማር. 10፥46-52)
35ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ በቀረበ ጊዜ አንድ ዕውር ምጽዋት እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር፤ 36በአጠገቡ የሚያልፉትን የብዙ ሰዎች ድምፅ በሰማ ጊዜ “ይህ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ።
37ሰዎቹም “እነሆ! የናዝሬቱ ኢየሱስ በዚህ በኩል እያለፈ ነው” ብለው ነገሩት።
38በዚያን ጊዜ ዐይነ ስውሩ፥ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ! እባክህ ማረኝ!” እያለ ጮኸ።
39ቀድመው እፊት እፊት ይሄዱ የነበሩት ሰዎች፦ “ዝም በል!” ብለው ገሠጹት። እርሱ ግን ድምፁን በይበልጥ ከፍ አድርጎ፦ “የዳዊት ልጅ ሆይ! እባክህ ማረኝ!” ይል ነበር።
40ስለዚህ ኢየሱስ ቆመና “ወደ እኔ አምጡት” ብሎ አዘዘ። ዐይነ ስውሩም ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ፥ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ 41“ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?”
ዐይነ ስውሩም “ጌታ ሆይ! ማየት እፈልጋለሁ” አለው።
42ኢየሱስም “እይ! እምነትህ አድኖሃል” አለው።
43ዐይነ ስውሩም ወዲያውኑ ማየት ቻለ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ኢየሱስን መከተል ጀመረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ይህን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

Markering

Del

Kopiér

None

Vil du have dine markeringer gemt på tværs af alle dine enheder? Tilmeld dig eller log ind