የሉቃስ ወንጌል 17

17
ለሰው መሰናክል ከመሆን መጠንቀቅ
(ማቴ. 18፥6-721-22ማር. 9፥42)
1ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ሰዎችን አሰናክለው ወደ ኃጢአት የሚጥሉ ነገሮች መምጣታቸው አይቀርም፤ ነገር ግን የኃጢአትን መሰናክል ለሚያመጣው ለዚያ ሰው ወዮለት! 2ማንም ሰው ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን ከሚያሰናክል ይልቅ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር። 3ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ! ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው! በበደሉ ከተጸጸተም ይቅር በለው! #ማቴ. 18፥15። 4በቀን ሰባት ጊዜ ቢበድልህና በቀን ሰባት ጊዜም ወደ አንተ እየመጣ ‘በበደሌ ተጸጽቼአለሁ’ ቢልህ ይቅር በለው።”
5ሐዋርያቱም ጌታ ኢየሱስን “እባክህ እምነት ጨምርልን” አሉት። 6ጌታ ኢየሱስም “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያኽል እምነት ቢኖራችሁ ይህን የሾላ ዛፍ ‘ከዚህ ተነቅለህ በባሕር ውስጥ ተተከል!’ ብትሉት ይታዘዝላችኋል” አላቸው።
የአገልጋይ ግዳጅ
7ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ አንዱ በእርሻ ሥራ የተሰማራ፥ ወይም በጎች የሚጠብቅ አገልጋይ ቢኖረው፥ አገልጋዩ ከሥራው በተመለሰ ጊዜ ወዲያውኑ ‘ና ተቀመጥና ራትህን ብላ’ ይለዋልን? 8ይልቅስ፥ ‘በል! ራቴን አዘጋጅልኝ፤ እስክበላና እስክጠጣም አደግድገህ አገልግለኝ፤ ከዚህ በኋላ አንተ ደግሞ ትበላለህ፥ ትጠጣለህ’ ይለው የለምን? 9ታዲያ፥ አገልጋዩ የታዘዘውን ስለ ፈጸመ ጌታው የሚያመሰግነው ይመስላችኋልን? 10እናንተም እንዲሁ የታዘዛችሁትን ሁሉ በፈጸማችሁ ጊዜ፥ ‘የማንጠቅም አገልጋዮች ነን፤ የፈጸምነውም ግዳጃችንን ብቻ ነው’ በሉ።”
ኢየሱስ ዐሥር ለምጻሞችን እንደ ፈወሰ
11ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በሰማርያና በገሊላ መካከል ያልፍ ነበር፤ 12ወደ አንዲት መንደርም በገባ ጊዜ ዐሥር ለምጻሞች ወደ እርሱ መጥተው በሩቅ ቆሙ፤ 13ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ኢየሱስ ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ እባክህ ማረን!” እያሉ ጮኹ።
14ኢየሱስም አያቸውና “ሂዱ! ሰውነታችሁን ለካህናት አሳዩ!” አላቸው፤ #ዘሌ. 14፥1-32።
እነርሱም በመሄድ ላይ ሳሉ ከለምጻቸው ነጹ። 15ከእነርሱም አንዱ ከለምጹ መንጻቱን ባየ ጊዜ በከፍተኛ ድምፅ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ተመለሰ። 16ኢየሱስንም እያመሰገነ በእግሩ ሥር በግምባሩ ተደፋ፤ እርሱ የሰማርያ ሰው ነበር። 17ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከለምጽ የነጹት ሰዎች ዐሥር አልነበሩምን? ታዲያ፥ ዘጠኙ የት አሉ? 18እግዚአብሔርን ለማመስገን ተመልሶ የመጣ ከዚህ ከባዕድ ሰው በቀር ሌላ አንድም አልተገኘምን?” 19ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው፦ “ተነሥና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።
የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት
(ማቴ. 24፥23-2837-41)
20ፈሪሳውያን ኢየሱስን፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ሲሉ ጠየቁት፤ እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት የምትመጣው ሰዎች ነቅተው በሚጠባበቁት ዐይነት አይደለም፤ 21እንዲሁም ‘እነሆ፥ እዚህ ናት ወይም እዚያ ናት’ የምትባል አይደለችም፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ነች።”
22ቀጥሎም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትናፍቁበት ቀን ይመጣል፤ ነገር ግን አታዩም። 23ሰዎች ‘እነሆ፥ ክርስቶስ እዚህ ነው! ወይም እዚያ ነው!’ ይሉአችኋል፤ ነገር ግን አትሂዱ፤ አትከተሉአቸውም። 24መብረቅ በሰማይ ላይ ሲበርቅ ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ የሰው ልጅ በሚመጣበትም ቀን እንዲሁ ይሆናል፤ 25ነገር ግን የሰው ልጅ አስቀድሞ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ በዚህ ትውልድም ሊናቅና ሊነቀፍ ግድ ነው። 26በኖኅ ዘመን እንደሆነው ዐይነት የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜም እንዲሁ ይሆናል። #ዘፍ. 6፥5-8። 27ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያገቡና ሲጋቡም ነበር፤ በዚያን ጊዜ የጥፋት ውሃ መጣና አጥለቅልቆ ሁሉንም አጠፋቸው። #ዘፍ. 7፥6-24። 28እንዲሁም ደግሞ በሎጥ ዘመን እንደሆነው ዐይነት ይሆናል፤ በዚያን ጊዜ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲሸጡና ሲገዙ፥ አትክልት ሲተክሉና ቤትም ሲሠሩ ነበር። 29ነገር ግን ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ ሁሉንም አጠፋቸው፤ 30የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀንም እንዲሁ ይሆናል።
31“በዚያን ቀን በቤቱ ጣራ ላይ ያለ ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ዕቃ ለመውሰድ አይውረድ፤ በእርሻም ቦታ ያለ ሰው ወደ ቤቱ አይመለስ። #ማቴ. 24፥17-18፤ ማር. 13፥15-16። 32የሎጥን ሚስት አስታውሱ! #ዘፍ. 19፥26። 33ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሁሉ ያድናታል። #ማቴ. 10፥39፤ 16፥25፤ ሉቃ. 9፥24፤ ዮሐ. 12፥25። 34በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይተኛሉ፤ ከእነርሱም አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል እላችኋለሁ። 35ሁለት ሴቶች በአንድ ቦታ አብረው ይፈጫሉ፤ አንድዋ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ ትቀራለች። [ 36ሁለት ሰዎች በአንድ እርሻ ቦታ ይሠራሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።”] #17፥36 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች ቊ. 36 ይጨምራሉ፤ እርሱም በማቴ. 24፥40 ያለውን ይመስላል።
37ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስን፥ “ጌታ ሆይ፥ ወዴት ነው የሚወሰዱት” ሲሉ ጠየቁት።
እርሱም “በድን ባለበት አሞራዎች ይሰበሰባሉ” ሲል መለሰላቸው።

Markering

Del

Kopiér

None

Vil du have dine markeringer gemt på tværs af alle dine enheder? Tilmeld dig eller log ind