የዮሐንስ ወንጌል 5
5
ጌታችን መፃጕዕን እንደ ፈወሰው
1ከዚህም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 2በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል፤ አምስት እርከኖችም ነበሩአት። 3በዚያም ዕውሮችና አንካሶች፥ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃዉን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር። 4የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያዉ ወርዶ ውኃዉን በሚያናውጠው ጊዜ፥ ከውኃዉ መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበርና። 5በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር። 6ጌታችን ኢየሱስም ያን ሰው በአልጋዉ ተኝቶ ባየ ጊዜ በደዌ ብዙ ዘመን እንደ ቈየ ዐውቆ፥ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው። 7ድውዩም መልሶ፥ “አዎን ጌታዬ ሆይ፥ ነገር ግን ውኃዉ በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያዉ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው። 8ጌታችን ኢየሱስም፥ “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። 9ወዲያውኑም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ያች ቀንም ሰንበት ነበረች።
10 #
ነህ. 13፥19፤ ኤር. 17፥21። አይሁድም የዳነውን ሰው፥ “ዛሬ ሰንበት ነው፤ አልጋህን ልትሸከም አይገባህም” አሉት። 11እርሱም መልሶ፥ “ያዳነኝ እርሱ፦ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” አላቸው። 12አይሁድም፥ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?” ብለው ጠየቁት። 13ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ነበርና። 14ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና፥ “እነሆ፥ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” አለው። 15ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው። 16ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና። 17ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ” አላቸው። 18ስለዚህም አይሁድ ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፤ “ሰንበትን የሚሽር ነው” በማለት ብቻ አይደለም፤ ደግሞም እግዚአብሔርን “አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል” በማለት ነው እንጂ።
19ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል። 20አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል። 21አብ ሙታንን እንደሚያስነሣቸው፥ ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል። 22አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ። 23ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም። 24እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ በላከኝም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛል፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይሄድም።
25“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ቃል የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም ይድናሉ። 26ለአብ በራሱ ሕይወት እንዳለው፥ እንዲሁም ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጠው። 27የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ነውና ይፈርድ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠው።
ስለ ትንሣኤ ሙታን
28“በመቃብር ያሉ ሁሉ ቃሉን የሚሰሙባት ጊዜ ትመጣለችና ስለዚህ አታድንቁ። 29#ዳን. 12፥2። መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፥ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ። 30እኔ ከራሴ አንዳች አደርግ ዘንድ አልችልም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ እንጂ፤ ፍርዴም እውነት ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የእኔን ፈቃድ አልሻምና።
ስለ ምስክርነት
31“እኔ ለራሴ ብመሰክር ምስክርነቴ እውነት አይደለም። 32ነገር ግን ለእኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፤ ስለ እኔ የመሰከረው ምስክርነቱም እውነት እንደሆነ አውቃለሁ። 33#ዮሐ. 1፥19-27፤ 3፥27-30። እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችሁ አልነበረምን? እርሱም ምስክርነቱን በእውነት ነገራችሁ። 34እኔ ግን የሰውን ምስክርነት የምሻ አይደለሁም፤ ነገር ግን እናንተ ትድኑ ዘንድ ይህን እላለሁ። 35እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፤ እናንተም አንዲት ሰዓት በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ። 36እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ ልሠራውና ልፈጽመው አባቴ የሰጠኝ ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ያ የምሠራው ሥራ ምስክሬ ነውና። 37#ማቴ. 3፥17፤ ማር. 1፥11፤ ሉቃ. 3፥22። የላከኝ አብም ስለ እኔ መስክሮአል፤ ከሆነም ጀምሮ ቃሉን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም። 38ቃሉም የላችሁም፤ በእናንተ ዘንድም አይኖርም፤ እርሱ የላከውን አላመናችሁምና። 39መጻሕፍትን መርምሩ፤ በእነርሱ የዘለዓለም ሕይወትን የምታገኙ ይመስላችኋልና፤ እነርሱም የእኔ ምስክሮች ናቸው። 40ሕይወትን ታገኙ ዘንድ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። 41እኔ ከሰው ክብርን ልቀበል አልሻም። 42ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በእናንተ እንደሌለባችሁ ዐወቅሁ። 43እኔ በአባቴ ስም መጣሁ፥ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው ግን በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ። 44ከባልንጀራችሁ ክብርን የምትመርጡ፥ ከአንድ እግዚአብሔርም ክብርን የማትሹ እናንተ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? 45እኔ በአብ ዘንድ የምከስሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከስሳችሁስ አለ፤ እርሱም እናንተ ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው። 46ሙሴንስ አምናችሁት ቢሆን እኔንም ባመናችሁኝ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። 47ሙሴ የጻፈውን ካላመናችሁ ግን የእኔን ቃል እንዴት ታምናላችሁ?”
Právě zvoleno:
የዮሐንስ ወንጌል 5: አማ2000
Zvýraznění
Sdílet
Kopírovat
Chceš mít své zvýrazněné verše uložené na všech zařízeních? Zaregistruj se nebo se přihlas