ኦሪት ዘፍጥረት 9
9
ምዕራፍ 9
እግዚአብሔር ለኖኅ የሰጠው ቃል ኪዳን
1እግዚአብሔርም ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “ብዙ፤ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሉአት፤ ግዙአትም። 2አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በምድር አራዊት፥ በሰማይ ወፎች፥ በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱትም፥ በባሕር ዓሦችም ሁሉ ላይ ይሁን፤ እነርሱንም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ። 3ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ መብል ይሁናችሁ፤ ሁሉንም እንደ ለመለመ ቡቃያ ሰጠኋችሁ። 4ነገር ግን ደመ ነፍስ ያለበትን ሥጋ አትብሉ፤ 5ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን ከአራዊት ሁሉ እጅ እሻዋለሁ፤ ከሰውም እጅ፥ ከሰው ወንድም እጅ፥ የሰውን ነፍስ እሻለሁ። 6የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ስለዚያ ደም ፈንታ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሬዋለሁና። 7እናንተም ብዙ፤ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሉአት፤ ግዙአትም።”
8እግዚአብሔርም ለኖኅ፥ ከእርሱም ጋር ለልጆቹ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ 9“እኔም እነሆ፥ ቃል ኪዳኔን ከእናንተ ጋር፥ ከእናንተም በኋላ ከዘራችሁ ጋር አጸናለሁ፤ 10ከእናንተ ጋር ላሉትም፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ሁሉ፥ ከእናንተ ጋር ከመርከብ ለወጡት ለወፎች፥ ለእንስሳትም፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ፥ ለማንኛውም ለምድር አራዊት ሁሉ ይሆናል። 11ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ፤ ሥጋ ያለውም ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም።” 12እግዚአብሔር አምላክም ለኖኅ አለው፥ “በእኔና በእናንተ መካከል፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል፥ ለዘለዓለም ትውልድ የማደርገው የቃል ኪዳኔ ምልክት ይህ ነው፤ 13ቀስቴን በደመና አኖራለሁ፤ የቃል ኪዳኔም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል። 14በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቴ በደመናው ትታያለች፤ 15በእኔና በእናንተ መካከል፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃን አላመጣም። 16ቀስቴም በደመና ትሆናለች፤ በእኔና በምድር መካከል፥ በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘለዓለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ።” 17እግዚአብሔርም ኖኅን፥ “በእኔና በምድር ላይ በሚኖር፥ ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያጸናሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው” አለው።
ኖኅና ልጆቹ
18ከመርከብ የወጡት የኖኅ ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ሴም፥ ካም፥ ያፌት፤ ካምም የከነዓን አባት ነው። 19በምድር ሁሉ ላይ የተበተኑ የኖኅ ልጆች እነዚህ ሦስቱ ናቸው።
20ኖኅም ገበሬ መሆን ጀመረ፤ ወይንም ተከለ። 21ከወይን ጠጁም ጠጣና ሰከረ፤ በድንኳኑም ውስጥ ዕራቁቱን ሆነ። 22የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፤ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። 23ሴምና ያፌትም ልብስ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፤ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበር፤ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም። 24ኖኅም ከወይኑ ስካር በነቃ ጊዜ፥ ታናሹ ልጁ ያደረገበትን ዐወቀ።
25ኖኅም እንዲህ አለ፥ “ከነዓን ርጉም ይሁን፤ ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን።” 26እንዲህም አለ፥ “የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፤ ከነዓንም ለእርሱ ባሪያ ይሁን። 27እግዚአብሔር የያፌትን ሀገር ያስፋ፤ በሴምም ድንኳን ይደር፤ ከነዓንም ለእርሱ ባሪያ ይሁን።”
28ኖኅም ከጥፋት ውኃ በኋላ ሦስት መቶ አምሳ ዓመት ኖረ። 29ኖኅም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አምሳ ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
S'ha seleccionat:
ኦሪት ዘፍጥረት 9: አማ2000
Subratllat
Comparteix
Copia
Vols que els teus subratllats es desin a tots els teus dispositius? Registra't o inicia sessió