መጽሐፈ ኢዮብ 3
3
1ከዚያም በኋላ ኢዮብ አፉን ከፍቶ የተወለደበትን ቀን ረገመ። 2ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦
3ያ የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ፥
ያም፦ ወንድ ልጅ ተፀነሰ የተባለበት ሌሊት።
4ያ ቀን ጨለማ ይሁን፥
እግዚአብሔር ከላይ አይመልከተው፥
ብርሃንም አይብራበት።
5ጨለማና የሞት ጥላ የራሳቸው ገንዘብ ያድርጉት፥
ዳመናም ይረፍበት፥
የቀን ጨለማ ሁሉ ያስፈራው።
6ያን ሌሊት ጨለማ ይያዘው፥
በዓመቱ ቀኖች መካከል ደስ አይበለው፥
በወሮች ውስጥ ገብቶ አይቈጠር።
7እነሆ፥ ያ ሌሊት መካን ይሁን፥
እልልታ አይግባበት።
8ሌዋታንን ለማንቀሳቀስ የተዘጋጁ
ቀኑን የሚረግሙ ይርገሙት።
9አጥቢያ ኮከቦች ይጨልሙ፥
ብርሃንን ቢጠባበቅ አያግኘው፥
የንጋትንም ቅንድብ አይይ፥
10የእናቴን ማኅፀን ደጅ አልዘጋምና፥
መከራንም ከዓይኔ አልሰወረምና።
11በማኅፀን ሳለሁ ስለ ምን አልሞትሁም?
ከሆድስ በወጣሁ ጊዜ ፈጥኜ ስለ ምን አልጠፋሁም?
12ጕልበቶች ስለ ምን ተቀበሉኝ?
ጡትስ ስለ ምን ጠባሁ?
13አሁን ተኝቼ ዝም ባልሁ ነበር፥
አንቀላፍቼ ባረፍሁ ነበር፥
14የፈረሰውን ለራሳቸው ከሚሠሩት
ከምድር ነገሥታትና መካሮች ጋር፥
15ወይም ቤታቸውን ብር ከሞሉ
ወርቅም ካላቸው መኳንንት ጋር፥
16ወይም እንደ ተቀበረ ጭንጋፍ፥
ብርሃንም እንዳላዩ ሕፃናት በሆንሁ ነበር።
17ክፉዎች በዚያ መናደዳቸውን ይተዋሉ፥
በዚያም ደካሞች ያርፋሉ።
18በዚያ ግዞተኞች በአንድነት ተዘልለው ተቀምጠዋል፥
የአስጨናቂውን ድምፅ አይሰሙም።
19ታናሽና ታላቅ በዚያ አሉ፥
ባሪያም ከጌታው ነጻ ወጥቶአል።
20በመከራ ላሉት ብርሃን፥
ነፍሳቸው መራራ ለሆነችባቸው፥
21የተሰወረ ሀብትን ከሚቈፍሩ ይልቅ
ሞትን ለሚጠብቁ ለማያገኙትም፥
22መቃብርን ባገኙ ጊዜ
በእልልታ ደስ ለሚላቸው፥ ሐሤትንም ለሚያደርጉ
ሕይወት ስለ ምን ተሰጠ?
23መንገዱ ለተሰወረበት ሰው፥
እግዚአብሔርም በአጥር ላጠረው
ብርሃን ስለ ምን ተሰጠ?
24ከእንጀራዬ በፊት ልቅሶዬ መጥቶአልና፥
ጩኸቴም እንደ ውኃ ፈስሶአል።
25የፈራሁት ነገር መጥቶብኛልና፥
የደነገጥሁበትም ደርሶብኛል።
26ተዘልዬ አልተቀመጥሁም፥ አልተማመንሁም፥ አላረፍሁም፥
ነገር ግን መከራ መጣብኝ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 3: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in