መጽሐፈ ኢዮብ 2
2
1ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፥ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣን ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም በመካከላቸው መጣ። 2እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም፦ በምድር ላይ ዞርሁ፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። 3እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም፥ በከንቱም አጠፋው ዘንድ አንተ በእርሱ ላይ ምንም ብታንቀሳቅሰኝ፥ እስከ አሁን ፍጹምነቱን ይዞአል። 4ሰይጣንም መልሶ እግዚአብሔርን፦ ቁርበት ስለ ቁርበት ነው፥ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል። 5ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳብስ፥ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል አለው። 6እግዚአብሔም ሰይጣንን፦ ሕይወቱን ተወው እንጂ እነሆ፥ እርሱ በእጅህ ነው አለው።
7ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፥ ኢዮብንም ከእግሩ ጫማ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቍስል መታው። 8ሥጋውንም ይፍቅበት ዘንድ ገል ወሰደ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ። 9ሚስቱም፦ እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት አለችው።
(የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።)
ዳግመኛ እግዚአብሔርን ጥቂት ወራት ደጅ እጠናዋለሁ፥ ዳግመኛም መከራውን እታገሠዋለሁ የቀድሞ ኑሮዬንም ተስፋ አደርገዋለሁ ትላለህን? አለችው። እንደዚህሳ እንዳትል ከዚህ ዓለም እነሆ ስም አጠራርህ ጠፋ፥ ሴቶች ልጆቼና ወንዶች ልጆቼም ሞቱ እኔስ ዘጠኝ ወር ሳረግዝ ሳምጥ ስወልድ ሳይረቡኝ ሳይጠቅሙኝ በከንቱ ደከምሁ አለች። አንተም በመግል ተውጠህ በትል ተከብበህ ትኖራለህ፥ ሌሊቱን ሁሉ ስትዛብር ታድራለህ። እኔ ግን እየዞርሁ እቀላውጣለሁ። ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እሄዳለሁ፥ ከድካሜ በእኔ ላይ ካለ ከችግሬም አርፍ ዘንድ ከጧት ጀምሮ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ እጠብቃለሁ፥ አሁን ግን እግዚአብሔርን የማይገባ ቃል ተናግረኸው ሙት አለች። 10እርሱ ግን፦ አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፥ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን? አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።
11ሦስቱም የኢዮብ ወዳጆች ይህን የደረሰበትን ክፉ ነገር ሁሉ ሰምተው ከየአገራቸው መጡ፥ እነርሱም ቴማናዊው ኤልፋዝ፥ ሹሐዊው በልዳዶስ፥ ነዕማታዊው ሶፋር ነበሩ። እነርሱም ሊያዝኑለትና ሊያጽናኑት በአንድነት ወደ እርሱ ለመምጣት ተስማሙ። 12ከሩቅም ሆነው ዓይናቸውን ባነሡ ጊዜ አላወቁትም፥ ድምፃቸውንም አሰምተው አለቀሱ፥ እያንዳንዳቸውም መጐናጸፊያቸውን ቀደዱ፥ ወደ ላይም ወደ ራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ። 13ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊትም ከእርሱ ጋር በምድር ላይ ተቀመጡ፥ ሕመሙም እጅግ እንደ በዛ አይተዋልና ከእነርሱ አንድ ቃል የሚናገረው አልነበረም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 2: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in