YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢዮብ 1

1
1ዖፅ በሚባል አገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፥ ያም ሰው ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ነበረ። 2ሰባትም ወንዶች ሦስትም ሴቶች ልጆች ተወልደውለት ነበር። 3ሀብቱም ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህም ግመሎች፥ አምስት መቶም ጥማድ በሬ፥ አምስት መቶም እንስት አህዮች ነበረ፥ እጅግ ብዙም ባሪያዎች ነበሩት፥ ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ። 4-5ወንዶች ልጆቹም ሄደው በየተራ በያንዳንዳቸው ቤት ግብዣ ያደርጉ ነበር፥ ሦስቱ እኅቶቻቸውም ከእነርሱ ጋር ይበሉና ይጠጡ ዘንድ እነርሱ ልከው ይጠሩአቸው ነበር። የግብዣውም ቀኖች ባለፉ ጊዜ ኢዮብ፦ ምናልባት ልጆቼ በድለው፥ እግዚአብሔርንም በልባቸው ሰድበው ይሆናል ብሎ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፥ ኢዮብም ማልዶ ተነሣ፥ እንደ ቍጥራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። እንዲሁ ኢዮብ ሁልጊዜ ያደርግ ነበር።
6ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፥ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ። 7እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም፦ ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። 8እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም አለው። 9ሰይጣንም ለእግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን? 10እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱም በምድር ላይ በዝቶአል። 11ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፥ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል። 12እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፥ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ አለው። ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ።
13አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፥ የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር። 14መልክተኛም ወደ ኢዮብ መጥቶ፦ በሬዎች እርሻ ያርሱ፥ በአጠገባቸውም አህዮች ይሰማሩ ነበር፥ 15የሳባም ሰዎች አደጋ ጣሉ፥ ወሰዱአቸውም፥ ብላቴኖቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው። 16እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ፦ የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወደቀች፥ በጎቹንም አቃጠለች፥ ጠባቂዎችንም በላች፥ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው። 17እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ፦ ከለዳውያን በሦስት ረድፍ ተከፍለው በግመሎች ላይ አደጋ ጣሉ፥ ወሰዱአቸውም፥ ብላቴኖቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው። 18እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ፦ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር፥ 19እነሆም፥ ዐውሎ ነፋስ ከምድረ በዳ መጥቶ የቤቱን አራቱን ማዕዘን መታው፥ በብላቴኖቹም ላይ ወደቀ፥ ሞቱም፥ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው። 20ኢዮብም ተነሣ መጐናጸፊያውንም ቀደደ፥ ራሱንም ተላጨ፥ በምድርም ላይ ተደፍቶ ሰገደ፥ 21እንዲህም አለ፦ ራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ፥ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፥ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን። 22በዚህ ሁሉ ኢዮብ አልበደለም፥ ለእግዚአብሔርም ስንፍናን አልሰጠም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in