ትንቢተ ኤርምያስ 19
19
1እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ሂድ፥ ከሸክላ ሠሪ ገምቦ ግዛ፥ ከሕዝቡም ሽማግሌዎችና ከካህናት ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፥ 2በካርሲት በር መግቢያ አጠገብ ወዳለው ወደ ሄኖም ልጅ ሸለቆ ሂድ፥ በዚያም የምነግርህን ቃል ተናገር፥ 3እንዲህም በል፦ የይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሰማውን ሰው ጆሮ ጭው የሚያደርግ ክፉ ነገር፥ እነሆ፥ በዚህ ስፍራ አመጣለሁ። 4ትተውኛልና፥ ይህንም ስፍራ እንግዳ አድርገውታልና፥ እነርሱና አባቶቻቸውም ለማያውቋቸው ለሌሎች አማልክት ዐጥነዋልና የይሁዳም ነገሥታት ይህን ስፍራ በንጹህ ደም ሞልተዋልና፥ 5እኔም ያላዘዝሁትን ያልተናገርሁትንም ወደ ልቤም ያልገባውን፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አድርገው ለበኣል ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ የበኣልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠርተዋልና ስለዚህ፥ 6እነሆ፥ ይህ ስፍራ የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 7በዚህም ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምክር አፈርሳለሁ፥ በጠላቶቻቸውም ፊት በሰይፍና ነፍሳቸውን በሚሹት እጅ እጥላቸዋለሁ፥ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ። 8ይህችንም ከተማ ለመደነቂያና ለማፍዋጫ አደርጋታለሁ፥ የሚያልፍባትም ሁሉ ስለ ተደረገባት መቅሠፍት ሁሉ ይደነቃል ከንፈሩንም ይመጥጣል። 9የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውንም ሥጋ አበላቸዋለሁ፥ ሁሉም ጠላቶቻቸውንና ነፍሳቸውን የሚሹት በሚያስጨንቋቸው ጭንቀትና መከበብ የባልንጀሮቻቸውን ሥጋ ይበላሉ።
10ገምቦውንም ከአንተ ጋር በሚሄዱ ሰዎች ፊት ትሰብራለህ፥ 11እንዲህም ትላቸዋለህ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሸክላ ሠሪው ዕቃ እንደሚሰባበር ደግሞም ይጠገን ዘንድ እንደማይቻል፥ እንዲሁ ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ እሰብራለሁ፥ የሚቀብሩበትም ስፍራ ሌላ የለምና በቶፌት ይቀበራሉ። 12እንዲሁ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ አደርጋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ይህችንም ከተማ እንደ ቶፌት አደርጋለሁ። 13የረከሱትም የኢየሩሳሌም ቤቶችና የይሁዳ ነገሥታት ቤቶች፥ እነዚያ በሰገነታቸው ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ ያጠኑባቸው ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቍርባን ያፈሰሱባቸው ቤቶች ሁሉ፥ እንደ ቶፌት ስፍራ ይሆናሉ።
14ኤርምያስም እግዚአብሔር ትንቢት ሊናገር ወደዚያ ልኮት ከነበረው ስፍራ ከቶፌት መጣ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አደባባይ ቆሞ ለሕዝብ ሁሉ፦ 15የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቃሌን እንዳይሰሙ አንገታቸውን አደንድነዋልና እነሆ፥ በዚህች ከተማና በመንደሮችዋ ሁሉ ላይ የተናገርሁባትን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 19: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in