ትንቢተ ኤርምያስ 18
18
1-2ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል፥ እንዲህም አለው፦ ተነሥተህ ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ውረድ፥ በዚያም ቃሌን አሰማሃለሁ። 3ወደ ሸክላ ሠሪው ቤትም ወረድሁ፥ እነሆም፥ ሥራውን በመንኰራኵር ላይ ይሠራ ነበር። 4ከጭቃም ይሠራው የነበረ ዕቃ በሸክላ ሠሪው እጅ ተበላሸ፥ ሸክላ ሠሪውም እንደ ወደደ መልሶ ሌላ ዕቃ አድርጎ ሠራው።
5የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 6የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ይህ ሸክላ ሠሪ እንደሚሠራ በውኑ እኔ በእናንተ ዘንድ መሥራት አይቻለኝምን? እነሆ፥ ጭቃው በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ፥ እንዲሁ እናንተ በእኔ እንጅ አላችሁ። 7ስለ ሕዝብ ስለ መንግሥትም እነቅል አፈርስም አጠፋም ዘንድ በተናገርሁ ጊዜ፥ 8ይህ ስለ እርሱ የተናገርሁበት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፥ እኔ አደርግበት ዘንድ ካሰብሁት ክፉ ነገር እጸጸታለሁ። 9ስለ ሕዝቡም ስለ መንግሥትም እሠራውና እተክለው ዘንድ በተናገርሁ ጊዜ፥ 10በፊቴ ክፉን ነገር ቢያደርግ ቃሌንም ባይሰማ፥ እኔ አደርግለት ዘንድ ስለ ተናገርሁት መልካም ነገር እጸጸታለሁ። 11አሁን እንግዲህ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ክፉ ነገር እፈጥርባችኋለሁ፥ አሳብንም አስብባችኋለሁ፥ አሁንም ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፥ መንገዳችሁንና ሥራችሁንም አቅኑ ብለህ ተናገራቸው። 12እነርሱ ግን፦ እንጨክናለን፥ አሳባችንን ተከትለን እንሄዳለን ሁላችንም እንደ ክፉው ልባችን እልከኝነት እናደርጋለን አሉ።
13ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በአሕዛብ መካከል፦ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? ብላችሁ ጠይቁ። የእስራኤል ድንግል በጣም የሚያስደነግጠውን ነገር አድርጋለች። 14በውኑ የሊባኖስ በረዶ የምድረ በዳውን ድንጋይ ይተዋልን? ወይስ ከሩቅ የምትመጣው ቀዝቃዛይቱ ፈሳሽ ውኃ ትደርቃለችን? 15ሕዝቤ ግን ረስተውኛል ለከንቱ ነገርም ዐጥነዋል፥ ከመንገዱም ተሰናክለዋል ከቀድሞውም ጐዳና ርቀው ወዳልተሠራው ወደ ጠማማው መንገድ ፈቀቅ ብለዋል። 16ምድራቸውን ለመደነቂያና ለዘላለም ማፍዋጫ አድርገዋል፥ የሚያልፍባት ሁሉ ይደነቃል፥ ራሱንም ያነቃንቃል። 17በጠላት ፊት እንደ ምሥራቅ ነፋስ እበትናቸዋለሁ፥ በጥፋታቸውም ቀን ጀርባዬን እንጂ ፊቴን አላሳያቸውም።
18እነርሱም፦ ሕግ ከካህን፥ ምክርም ከጠቢብ፥ ቃልም ከነቢይ አይጠፋምና ኑ፥ በኤርምያስ ላይ አሳብን እናስብ። ኑ፥ በምላስ እንምታው፥ ቃሉንም ሁሉ አናድምጥ አሉ።
19አቤቱ፥ አድምጠኝ፥ የክርክሬንም ቃል ስማ። 20ለነፍሴ ጕድጓድ ቈፍረዋልና በውኑ በመልካም ፋንታ ክፉ ይመለሳልን? ስለ እነርሱ በመልካም እናገር ዘንድ ቍጣህንም ከእነርሱ እመልስ ዘንድ በፊትህ እንደ ቆምሁ አስብ። 21ስለዚህ ልጆቻቸውን ለራብ ስጥ፥ ለሰይፍም እጅ አሳልፈህ ስጣቸው፥ ሚስቶቻቸውም የወላድ መካንና መበለቶች ይሁኑ፥ ወንዶቻቸውም በሞት ይጥፉ፥ ጕልማሶቻቸውም በሰልፍ ጊዜ በሰይፍ ይመቱ። 22ሊይዙኝ ጕድጓድ ቆፍረዋልና፥ ለእግሮቼም ወጥመድ ሸሽገዋልና ድንገት በላያቸው ጭፍራ ባመጣህ ጊዜ ከቤታቸው ጩኸት ይሰማ። 23አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ይገድሉኝ ዘንድ በላዬ የመከሩትን ምክር ሁሉ ታውቃለህ፥ በደላቸውን ይቅር አትበል፥ ኃጢአታቸውንም ከፊትህ አትደምስስ፥ በፊትህም ይውደቁ፥ በቍጣህ ጊዜ እንዲሁ አድርግባቸው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 18: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in