YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መሳፍንት 18

18
1በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም። እስከዚያም ቀን ድረስ ለዳን ነገድ በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስት አልደረሳቸውም ነበርና በዚያ ዘመን የሚቀመጡባት ርስት ይሹ ነበር። 2የዳንም ልጆች ከወገናቸው አምስት ጽኑዓን ሰዎች ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲመረምሩ፦ ሂዱ ምድሪቱንም ሰልሉ ብለው ከጾርዓና ከኤሽታኦል ሰደዱ። እነዚያም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጥተው በዚያ አደሩ። 3በሚካ ቤት አጠገብም በነበሩ ጊዜ የሌዋዊውን የጕልማሳውን ድምፅ አወቁ፥ ወደ እርሱም ቀርበው፦ ወደዚህ ማን አመጣህ? በዚህስ የምታደርገው ምንድር ነው? በዚህስ ምን አለህ? አሉት። 4እርሱም፦ ሚካ እንዲህ እንዲህ አደረገልኝ፥ ቀጠረኝም፥ እኔም ካህን ሆንሁለት አላቸው። 5እነርሱም፦ የምንሄድበት መንገድ የቀና መሆኑን እናውቅ ዘንድ፥ እባክህ፥ እግዚአብሔርን ጠይቅልን አሉት። 6እርሱም፦ የምትሄዱበት መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና በደኅና ሂዱ አላቸው።
7አምስቱም ሰዎች ሄዱ ወደ ሌሳም መጡ፥ በውስጡም የነበሩትን ሕዝብ ተዘልለው አዩአቸው፥ አንደ ሲዶናውያንም ልማድ ጸጥ ብለው ተዘልለው ተቀምጠው ነበር፥ የሚያስቸግራቸውም የሚገዛቸውም አልነበረም፥ ከሲዶናውያንም ርቀው ከሰውም ሁሉ ተለይተው ለብቻቸው ይኖሩ ነበር። 8ወደ ወንድሞቻቸውም ወደ ጾርዓና ወደ ኤሽታኦል ተመለሱ፥ ወንድሞቻቸውም፦ ምን ወሬ ይዛችኋል? አሉአቸው። 9እነርሱም፦ ምድሪቱ እጅግ መልካም እንደ ሆነች አይተናልና ተነሡ፥ በእነርሱ ላይ እንውጣ፥ እናንተ ዝም ትላላችሁን? ትሄዱ ዘንድ ምድሪቱንም ለመውረስ ትገቡ ዘንድ ቸል አትበሉ። 10በሄዳችሁ ጊዜ ተዘልለው ወደ ተቀመጡ ሕዝብ ትደርሳላችሁ፥ ምድሪቱም ሰፊ ናት፥ እግዚአብሔርም በምድር ካለው ነገር ሁሉ አንዳች የማይጎድልበትን ስፍራ በእጃችሁ ሰጥቶአል አሉ።
11ከዳን ወገንም የጦር ዕቃ የታጠቁ ስድስት መቶ ሰዎች ከዚያ ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሥተው ሄዱ። 12ወጥተውም በይሁዳ ባለችው በቂርያትይዓሪም ሰፈሩ፥ ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የዳን ሰፈር ተብሎ ተጠራ፥ እነሆም፥ ከቂርያትይዓሪም በስተ ኋላ ነው። 13ከዚያም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር አለፉ፥ ወደ ሚካም ቤት መጡ።
14የሌሳን ምድር ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎችም ወንድሞቻቸውን፦ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ኤፉድና ተራፊም፥ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስልም እንዳሉ ታውቃላችሁን? አሁንም የምታደርጉትን ምከሩ ብለው ተናገሩአቸው። 15ከመንገዱም ፈቀቅ ብለው ጕልማሳው ሌዋዊ ወደ ነበረበት ወደ ሚካ ቤት መጡ፥ ደኅንነቱንም ጠየቁት። 16የጦር ዕቃ የታጠቁት፥ ከዳን ልጆችም የሆኑት ስድስት መቶ ሰዎች በደጃፉ አጠገብ ቆመው ነበር። 17ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ወጥተው ወደዚያ ገቡ፥ የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም ወሰዱ፥ ካህኑም የጦር ዕቃ ከታጠቁት ከስድስት መቶ ሰዎች ጋር በደጃፉ አጠገብ ቆሞ ነበር። 18እነዚህም ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም በወሰዱ ጊዜ፥ ካህኑ፦ ምን ታደርጋላችሁ? አላቸው። 19እነርሱም፦ ዝም በል፥ እጅህንም በአፍህ ላይ ጫን፥ ከእኛም ጋር መጥተህ አባትና ካህን ሁንልን፥ ለአንድ ሰው ቤት መሆን ወይስ በእስራኤል ዘንድ ለነገድና ለወገን ካህን መሆን ማናቸው ይሻልሃል? አሉት። 20ካህኑም በልቡ ደስ አለው፥ ኤፉዱንም ተራፊሙንም የተቀረጸውንም ምስል ወሰደ፥ በሕዝቡም መካከል ሄደ።
21እነርሱም ዞረው ሄዱ፥ ሕፃናቶችንና ከብቶችን ዕቃዎችንም በፊታቸው አደረጉ። 22ከሚካም ቤት በራቁ ጊዜ የሚካ ጐረቤቶች ተሰበሰቡ፥ የዳንንም ልጆች ተከትለው ደረሱባቸው። 23ወደ ዳንም ልጆች ጮኹ፥ የዳንም ልጆች ፊታቸውን መልሰው ሚካን፦ የምትጮኸው ምን ሆነህ ነው? አሉት። 24እርሱም፦ የሠራኋቸውን አማልክቴን ካህኑንም ይዛችሁ ሄዳችኋል፥ ሌላ ምን አለኝ? እናንተስ፦ ምን ሆነሃል እንዴት ትሉኛላችሁ? አለ። 25የዳንም ልጆች፦ የተቈጡ ሰዎች እንዳይወድቁብህ ነፍስህም የቤተ ሰቦችህም ነፍስ እንዳይጠፋብህ፥ ድምፅህን በእኛ መካከል አታሰማ አሉት። 26የዳንም ልጆች መንገዳቸውን ሄዱ፥ ሚካም ከእርሱ እንደ በረቱ ባየ ጊዜ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ።
27እነርሱም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ለእርሱ የነበረውን ካህን ይዘው ወደ ሌሳ፥ ጸጥ ብሎ ተዘልሎም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ፥ መጡ፥ በሰይፍም ስለት መቱአቸው፥ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉአት። 28ከተማይቱ ከሲዶና ራቅ ያለች ነበረችና፥ እነርሱም ከሌሎች ሰዎች ተለይተው ብቻቸውን ይኖሩ ነበርና የሚታደግ አልነበራቸውም። ሌሳም በቤትሮዖብ አጠገብ ባለች ሸለቆ ውስጥ ነበረች። ከተማይቱንም ሠርተው ተቀመጡባት። 29ከተማይቱንም ከእስራኤል በተወለደው በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሩአት፥ የከተማይቱም ስም አስቀድሞ ሌሳ ነበረ። 30የዳንም ልጆች የተቀረጸውን ምስል ለራሳቸው አቆሙ፥ የሙሴም ልጅ የጌርሳም ልጅ ዮናታን፥ እርሱና ልጆቹ የአገሩ ሰዎች እስከሚማረኩበት ቀን ድረስ የዳን ነገድ ካህናት ነበሩ። 31ሚካም ያደረገውን የተቀረጸ ምስል የእግዚአብሔር ቤት በሴሎ ባለበት ዘመን ሁሉ አቆሙ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in