YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መሳፍንት 19

19
1በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ በሌለበት ጊዜ በተራራማው በኤፍሬም አገር ማዶ የተቀመጠ ሌዋዊ ነበረ፥ ከቤተ ልሔምም ይሁዳ ቁባት አገባ። 2ቁባቱም አመነዘረችበት፥ ትታውም ወደ አባትዋ ቤት ወደ ቤተ ልሔም ይሁዳ ሄደች፥ በዚያም አራት ወር ተቀመጠች። 3ባልዋም ተነሣ፥ ከእርስዋም ዕርቅ ሽቶ ወደ ቤቱ ሊመልሳት ፍለጋዋን ተከትሎ ሄደ፥ ከእርሱም ጋር አንድ አሽከር ሁለትም አህዮች ነበሩ። እርስዋም ወደ አባትዋ ቤት አገባችው፥ አባትዋም ባየው ጊዜ ደስ ብሎት ተገናኘው። 4የብላቴናይቱም አባት አማቱ የግድ አለ፥ በቤቱም ሦስት ቀን ተቀመጠ፥ በሉም፥ ጠጡም፥ በዚያም አደሩ። 5በአራተኛውም ቀን ማልደው ተነሡ፥ እርሱም ለመሄድ ተነሣ፥ የብላቴናይቱም አባት አማቹን፦ ሰውነትህን በቁራሽ እንጀራ አበርታ፥ ከዚያም በኋላ ትሄዳለህ አለው። 6ተቀመጡም በአንድ ላይም በሉ ጠጡም፥ የብላቴናይቱም አባት ሰውዮውን፦ ዛሬ ደግሞ ከዚህ ለማደር፥ እባክህ፥ ፍቀድ፥ ልብህንም ደስ ይበለው አለው። 7ሰውዮውም ሊሄድ ተነሣ፥ አማቱ ግን የግድ አለው፥ ዳግመኛም በዚያ አደረ። 8በአምስተኛውም ቀን ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፥ የብላቴናይቱም አባት፦ እባክህ፥ ሰውነትህን አበርታ፥ ቀኑም እስኪዋገድ ድረስ ቆይ አለው። ሁለቱም በሉ። 9ሰውዮውም ከቁባቱና ከአሽከሩ ጋር ለመሄድ በተነሣ ጊዜ የብላቴናይቱ አባት አማቱ፦ እነሆ፥ ቀኑ ተዋግዶአል፥ በዚህ እደሩ፥ እነሆ፥ ቀኑ ለማለፍ ተዋግዶአል፥ ልባችሁ ደስ እንዲለው በዚህ እደሩ፥ ነገም ወደ ቤታችሁ እንድትደርሱ ማልዳችሁ መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ አለው።
10ሰውዮው ግን በዚያ ሌሊት ለማደር አልፈቀደም፥ ተነሥቶም ሄደ፥ ኢየሩሳሌምም ወደ ተባለች ወደ ኢያቡስ ፊት ለፊት ደረሰ። ከእርሱም ጋር ሁለት የተጫኑ አህዮች ነበሩ፥ ቁባቱም ከእርሱ ጋር ነበረች። 11ወደ ኢያቡስም በደረሱ ጊዜ መሸባቸው፥ አሽከሩም ጌታውን፦ ና፥ ወደዚህ ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ፥ እባክህ፥ እናቅና፥ በእርስዋም እንደር አለው። 12ጌታውም፦ ከእስራኤል ወገን ወዳልሆነች ወደ እንግዳ ከተማ አንገባም፥ እኛ ወደ ጊብዓ እንለፍ አለው። 13አሽከሩንም፦ ና፥ ከእነዚህ ስፍራ ወደ አንዱ እንቅረብ፥ በጊብዓ ወይም በራማ እንደር አለው። 14መንገዳቸውንም ይዘው ሄዱ፥ የብንያምም ነገድ በምትሆነው በጊብዓ አጠገብ ሳሉ ፀሐይ ገባችባቸው። 15በጊብዓም ገብተው ያድሩ ዘንድ ወደዚያ አቀኑ። በገባም ጊዜ ሊያሳድራቸው ማንም በቤቱ አልተቀበላቸውምና በከተማው አደባባይ ተቀመጡ።
16እነሆም፥ አንድ ሽማግሌ ከእርሻው ሥራ ወደ ማታ መጣ፥ ይህም ሰው ከተራራማው ከኤፍሬም አገር ነበረ በጊብዓም በእንግድነት ተቀምጦ ነበር፥ የዚያ አገር ሰዎች ግን ብንያማውያን ነበሩ። 17ዓይኑንም አንሥቶ መንገደኛውን በከተማው አደባባይ አየ፥ ሽማግሌውም፦ ወዴት ትሄዳለህ? ከወዴትስ መጣህ? አለው። 18እርሱም፦ እኛ ከቤተ ልሔም ይሁዳ ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ማዶ እናልፋለን፥ እኔ ከዚያ ነኝ፥ ወደ ቤተ ልሔምም ይሁዳ ሄጄ ነበር፥ አሁንም ወደ እግዚአብሔር ቤት እሄዳለሁ፥ በቤቱም የሚያሳድረኝ አጣሁ፥ 19ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፥ ለእኔና ለገረድህ ከባሪያዎችህም ጋር ላለው አሽከር እንጀራና የወይን ጠጅ አለን፥ አንዳችም አላጣንም አለው። 20ሽማግሌውም፦ ሰላም ከአንተ ጋር ይሁን፥ የምትሻውንም ሁሉ እኔ እሰጥሃለሁ፥ በአደባባይ ግን አትደር አለው። 21ወደ ቤቱም አስገባው፥ ለአህዮቹም ገፈራ ጣለላቸው፥ እግራቸውንም ታጠቡ፥ በሉም ጠጡም።
22ሰውነታቸውንም ደስ ባሰኙ ጊዜ ወስላቶች የሆኑ የከተማው ሰዎች ቤቱን ከበቡ በሩንም ይደበድቡ ነበር፥ ባለቤቱንም ሽማግሌውን፦ ወደ ቤትህ የገባውን ሰው እንድንደርስበት አውጣልን አሉት። 23ባለቤቱም ሽማግሌው ወደ እነርሱ ወጥቶ፦ ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር፥ እባካችሁ፥ አታድርጉ፥ ይህ ሰው ወደ ቤቴ ገብቶአልና እንደዚህ ያለ ኃጢአት አትሥሩ። 24ድንግል ልጄና የእርሱም ቁባት፥ እነሆ፥ አሉ፥ አሁንም አወጣቸዋለሁ፥ አዋርዱአቸው እንደ ወደዳችሁም አድርጉባቸው፥ ነገር ግን በዚህ ሰው ላይ እንደዚህ ያለ ኃጢአት አታድርጉ አላቸው። 25ሰዎቹ ግን ነገሩን አልሰሙም፥ ሰውዮውም ቁባቱን ይዞ አወጣላቸው፥ ደረሱባትም፥ ሌሊቱንም ሁሉ እስኪነጋ ድረስ አመነዘሩባት፥ ጎህ በቀደደም ጊዜ ለቀቁአት። 26ሴቲቱም ማለዳ መጣች፥ ጌታዋም ባለበት በሰውዮው ቤት ደጅ ወድቃ እስኪነጋ ድረስ በዚያ ቀረች።
27ጌታዋም ማለዳ ተነሣ የቤቱንም ደጅ ከፈተ፥ መንገዱንም ለመሄድ ወጣ፥ እነሆም ቁባቲቱ ሴት በቤቱ ደጃፍ ወድቃ፥ እጅዋም በመድረክ ላይ ነበረ። 28እርሱም፦ ተነሺ፥ እንሂድ አላት፥ እርስዋ ግን ሞታ ነበርና አልመለሰችም፥ በዚያን ጊዜ በአህያው ላይ ጫናት፥ ተነሥቶም ወደ ስፍራው ሄደ። 29ወደ ቤቱም በመጣ ጊዜ ካራ አነሣ፥ ቁባቱንም ይዞ ከአጥንቶችዋ መለያያ ላይ ለአሥራ ሁለት ቈራርጦ ወደ እስራኤል አገር ሁሉ ሰደደ። 30ያየም ሁሉ፦ የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አልተደረገም፥ አልታየምም፥ አስቡት፥ በዚህም ተመካከሩ፥ ተነጋገሩም ይባባል ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in