YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘፍጥረት 35

35
1እግዚአብሔርም ያዕቆብን አለው፦ ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጠልህ ለእግዚአብሔርም መሠውያውን አድርግ። 2ያዕቆብም ለቤተ ሰቡና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ እንዲህ አለ፦ እንግዶቹን አማልክት ከመካከላችሁ አስወግዱ ንጹሐንም ሁኑ ልብሳችሁን፥ ለውጡ፤ 3ተነሥተንም ወደ ቤቴል እንውጣ በዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር መሠውያን አደርጋለሁ። 4በእጃቸው ያሉትንም እንግዶችን አማልክት ሁሉ በጆሮአችው ያሉትን ጕትቾች ለያዕቆብ ሰጡት ያዕቆብም በሴኬም አጠገብ ካለችው የአድባር ዛፍ በታች ቀበራቸው ተነሥተውም ሄዱ፤ 5የእግዚአብሔር ፍርሃት በዙሪያቸው ባሉች ከተሞች ሁሉ ወደቀ የያዕቆብም ልጆች ለማሳደድ አልተከተሉአቸውም። 6ያዕቆብም እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩት ሰዎች ሁሉ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሎዛ መጡ እርስዋም ቤቴል ናት። 7በዚያንም ቦታ ስም ኤልቤቴል ብሎ ጠራው እርሱ ለወንድሙ ፊት በሸሸበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ተገልጣለት ነበርና 8የርብቃ ሞግዚት ዲቦራም ሞተች በቤቴልም ከአድባር ዛፍ በታች ተቀበረች፤ ስሙም አሎንባኩት ተብሎ ተጠራ።
9እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከሁለት ወንዞች መካከል ከሶርይ ከተመለስ በኍላ እንደ ገና ተገለጠለት ባረከውም። 10እግዚአብሔርም፦ ስምህ ያዕቆብ ነው ከእንግዲህም ወዲህ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ አለ፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። 11እግዚአብሔር አለው፦ ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ ብዛ ተባዛም ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ። 12ለአብርሃም ለይስሐቅም የሰጠኍትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ ከአንተም በኍላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጠለሁ። 13እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ። 14ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ቦታ የድንጋይ ሐውልት ተከለ የመጠጥ መሥዋዕትንም በእርሱ ላይ አፈሰሰ ዘይትንም አፈሰሰበት። 15ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ያን ቦታ ቤቴል ብሎ ጠራው።
16ከቤቴልም ተነሡ ወደ ኤፍራታም ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት በምጡም ተጨነቀች። 17ምጡም ባስጨነቅስት ጊዜ አዋላጂቱ፦ አትፍሪ ይኸኛው ደግሞ ወንድ ልጅ ይሆንሻልና አለቻት። 18እርስዋም ስትሞት ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ ስሙን ቤንኦኒ ብላ ጠራችው አባቱ ግን ብንያም አለው። 19ራሔልልም ሞተች ወደ ኤፍራታ በምትወሰድም መንገድ ተቀበረች እርስዋም ቤተልሔም ናት። 20ያዕቆብም በመቃብርዋ ላይ ሐውልት አቆመ እርሱም እስከ ዛሬ የራሔል የመቃብርዋ ሐውልት ነው። 21እስራኤልም ከዚያ ተነሣ ድንኳኑንም ከጋዴር ግንብ በስተ ወዲያ ተከለ። 22እስራኤልም በዚያች አገር በተቀመጠ ጊዜ ሮቤል ሄደ የአባቱንም ቁባት ባላን ተገናኛት እስራኤልም ሰማ።
23የያዕቆብም ልጆች አሥራ ሁለት ናቸው የልያ ልጆች የያዕቆብ በኵር ልጅ ሮቤል ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፤ 24የራሔል ልጆች ዮሴፍ፥ ብንይም፤ 25የራሔል ባርያ የባላ ልጆች፤ ዳን፥ ንፍታሌም፤ 26የልያ ባሪያ የዘለፋ ልጆችም ጋድ አሴር እነዚህ በሁለቱ ወንዞች መካከል በሶርያ የተወለዱለት የያዕቆብ ልጆች ናቸው። 27ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ አብርሃምን ይስሐቅ እንግዶች ሆነው ወደ ተቀመጡባት ወደ መምሬ ወደ ቂት ያትአርባቅ እርስዋም ኬብሮን ወደምትባለው መጣ።
28የይስሐቅም ዕድሜ መቶ ሰማንያ ዓመት ሆነ 29ይስሐቅም ነፍሱን ሰጠም፥ ሞተም ሸምግሎ ዕድሜንም ጠግቦ ወደ ወገኖቹ ተከማቸ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in