ኦሪት ዘፍጥረት 34
34
1ለያዕቆብ የወለደችለት የልያ ልጅ ዲናም የዚያን አገር ሴቶች ልጆችን ለማየት ወጣች። 2የአገሩ አለቃ የኤዊያዊ ሰው የኤሞር ልጅ ሴኬም አያት ወሰዳርም ከእርስዋም ጋር ተኛ አስነወራትም። 3ልቡናውም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈ ብላቴናይቱንም ወደዳት ልብዋንም ደስ በሚያስኛት ነገር ተናገራት። 4ሴኬምም አባቱን ኤሞርን፦ ይህችን ብላቴና አጋባኝ ብሎ ነገረው። 5ያዕቆብም ልጁን ዲናን እንዳስነወራት ሰማ፤ ልጆቹም ከከብቶቻቸው ጋር በምድረ በዳ ነበሩ፤ ያዕቆብም እስኪመጡ ድረስ ዝም አለ። 6የሴኬም አባት ኤሞርም ይነግረው ዘንድ ወደ ያዕቆብ ወጣ። 7የያዕቆብም ልጆች ይህንን በሰሙ ጊዜ ከምድረ በዳ መጡ የያዕቆብን ልጅ በመተኛቱ በእስራኤል ላይ ስንፍናን ስላደረገ አዘኑ እጅግም ተቈጡ እንዲህ አይደረግምን። 8ኤሞርም እንዲህ ብሎ ነገራቸው፦ ልጄ ሴኬም በልጃችሁ ፍቅር ልቡ ተነድፎአልና ሚስት እንድትሆነው እባካችሁ እርስዋን ስጡት። 9ጋብቾችም ሁኑን፤ ሴቶች ልጆች ስጡን እናንተም የእኛን ሴቶች ልጆች ውሰዱ። 10ከእኝም ጋር ተቀመጡ ምድሪቱም በፊታችሁ ናት ኑሩባት ነግዱም ግዙአትም። 11ሴኬምም አባትዋንና ወንድሞችዋን እንዲህ አለ፦ በፊታችሁ ሞገስን ባገኝ የምትሉኝን እሰጣለሁ። 12ብዙ ማጫን እጅ መንሻ አምጣ በሉኝ በነገራችሁኝም መጠን እሰጣለሁ ይህችን ብላቴና ግን አጋቡኝ። 13የያዕቆብም ልጆች ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኮል መለሱ እኅታቸውን ዲናን አርክሶአታልና፤ 14እንዲህም አሉአቸው፦ እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ለመስጠት ይህንን ነገር እናደርግ ዘንድ አይቻለንም ይህ ነውር ይሆንብናልና። 15እንደ እኛ ሆናችሁ ወንዶቻችሁን ሁሉ ብትገርዙ በዚህ ብቻ እሺ እንላችኍለን ሴቶች ልጆቻችን እንስጣችኍለን የእናንተንም 16ሴቶች ልጆች እንወስዳለን አንድ ሕዝብም ሆነን ከእናንተ ጋር እንኖራለን። 17ትገረዙ ዘንድ እኛን ባትሰሙ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።
18ነገራቸውም በኤሞር ልጅ በሴኬምን በኤሞር ዘንድ የተወደደ ሆነ። 19ብላቴናውም ያሉትን ያደርግ ዘንድ አልዘገየም የያዕቆብን ልጅ ወደዶአልና እርሱም በአባቱ ቤት ካሉት ሁሉ የከበረ ነበረ። 20ኤሞርና ሴኬም ልጁም ወደ ከተማቸው አደባባይ ገቡ ለከተማቸውም ሰዎች እንዲህ ብለው 21ነገሩ፦ እነዚህ ሰዎች በእኛ ዘንድ የሰላም ሰዎች ናቸው በምድራችን ይቀመጡ ይነግዱባትም እነሆም ምድሪቱ ሰፊ ናት ሴቶች ልጆቻቸውን እንውሰድ ለእነርሱም ሴቶች ልጆቻቸንን እንስጥ 22ነገር ግን አንድ ሕዝብ ሆነን ከእኛ ጋር ይቀመጡ ዘንድ በዚህ ነገር ብቻ እሺ ይሉናል እነርሱ እንደ ተገረዙ ወንዶቻችንን ሁሉ ብንገርዝ። 23ከብቶቻቸውም ያላቸውም ሁሉ እንስሶቻቸውም ሁሉ ለእኛ አይደሉምን? በዚህ ነገር ብቻ እሺ ያልናቸው እንደ ሆን ከእኛ ጋር ይቀመጣሉ። 24ከከተማይቱም አደባባይ የሚወጡ ሁሉ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን እሺ አሉ ከከተማይቱ አደባባይ የሚወጡት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ። 25ሦስተኛም ቀን በሆነ ጊዜ እጅግ ቆስለው ሳሉ የዲና ወንድሞች የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ እየራሳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ሳይፈሩ ወደ ከተማ ገቡ 26ወንዱንም ሁሉ ገደሉ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምንም በሰይፍ ገደሉ እኅታቸውን ዲናንም ከሴኬም ቤት ይዘው ወጡ። 27የያዕቆብም ልጆች እኅታቸውን ዲናን ሰለ አረከሱአት ወደ ሞቱት ገብተው ከተማይቱን ዘረፉ፤ 28በጎቻቸውንም ላሞቻቸውንም አህዮቻቸውንም በውጭም በከተማም ያለውን ወሰዱ 29ሀብታቸውን ሁሉ ሕፃናቶቻቸውንና ሴቶቻቸውንም፥ ሁሉ ማረኩ በቤት ያለውንም ሁሉ ዘረፉ። 30ያዕቆብም ሌዊንና ስሞዖንን እንዲህ አለ፦ በዚች አገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ እኔ በቁጥር ጥቂት ነኝ እነርሱ በእኔ ላይ ይስበሰቡና ይመቱኛል እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ 31እነርሱም፦ በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ያደርግባትን? አሉ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 34: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in