ኦሪት ዘዳግም 25
25
1በሰዎች መካከል ጠብ ቢሆን፥ ወደ ፍርድም ቢመጡ፥ ፈራጆችም ቢፈርዱባቸው፥ ጻድቁን፦ ደኅና ነህ፥ የበደለውንም፦ በደለኛ ነህ ይበሉአቸው። 2በደለኛውም መገረፍ ቢገባው እንዲገረፍ ፈራጁ በፊቱ በምድር ላይ ያጋድመው፤ የግርፋቱም ቁጥር እንደ ኃጢአቱ መጠን ይሁን። 3ግርፋቱም አርባ ይሁን፤ ከዚህ በላይ ጨምሮ ብዙ ግርፋት ቢገርፈው ወንድምህ በፊትህ ነውረኛ ይሆናልና ከዚህ በላይ አይጨመርበት። 4እህል የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር። 5ወንድማማቾች በአንድነት ቢቀመጡ፥ አንዱም ልጅ ሳይኖረው ቢሞት፥ የሞተው ሰው ሚስት ሌላ ሰው ታገባ ዘንድ ወደ ውጭ አትሂድ፤ ነገር ግን የባልዋ ወንድም ወደ እርስዋ ገብቶ እርስዋን ያግባ፥ ከእርስዋም ጋር ይኑር። 6የምዋቹ ስም ከእስራኤል ዘንድ እንዳይጠፋ ከእርስዋ የሚወለደው በኩር ልጅ በሞተው በወንድሙ ስም ይጠራ። 7ያም ሰው የወንድሙን ሚስት ማግባት ባይወድድ፥ ዋርሳይቱ በበሩ አደባባይ ወደሚቀመጡ ሽማግሌዎች ሄዳ፦ ዋርሳዬ በእስራኤል ዘንድ ለወንድሙ ስም ማቆም እንቢ አለ፤ ከእኔ ጋር ሊኖርም አልወደደም ትበላቸው። 8የከተማውም ሽማግሌዎች ጠርተው ይጠይቁት፤ እርሱም በዚያ ቆሞ፦ አገባት ዘንድ አልወድድም ቢል፥ 9ዋርሳይቱ በሽማግሌዎቹ ፊት ወደ እርሱ ቀርባ፦ የወንድሙን ቤት በማይሠራ ሰው ላይ እንዲህ ይደረግበታል ስትል ጭማውን ከእግሩ ታውጣ፥ በፊቱም እንትፍ ትበልበት። 10በእስራኤልም ዘንድ ስሙ የጫማ ፈቱ ቤት ተብሎ ይጠራ። 11ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ቢጣሉ፥ የአንደኛውም ሚስት ባልዋን ከሚመታው ሰው እጅ ታድነው ዘንድ ብትቀርብ፥ እጅዋንም ዘርግታ ብልቱን ብትይዝ፥ 12እጅዋን ቁረጥ፥ ዓይንህም አትራራላት። 13በከረጢትህ ውስጥ ታላቅና ታናሽ የሆነ ሁለት ዓይነት ሚዛን አይኑርልህ። 14በቤትህ ውስጥ ታላቅና ታናሽ የሆነ ሁለት ዓይነት መስፈሪያ አይኑርልህ። 15-16ይህን የሚያደርግ ሁሉ ክፋትንም የሚያደርግ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጣላ ነውና አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ እውነተኛና ፍጹም ሚዛን ይሁንልህ፤ እውነተኛና ፍጹም መስፈሪያም ይሁንልህ። 17ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ አማሌቅ በመንገድ ላይ ያደረገብህን አስብ፤ 18በመንገድ ላይ እንደ ተቃወመህ፥ አንተም ተስኖህ ደክመህም ሳለህ ከአንተ በኋላ ደክመው የነበሩትን ሁሉ እንደ መታ፤ እግዚአብሔርንም አልፈራም። 19ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር ከሚከብቡህ ጠላቶችህ ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ባሳረፈህ ጊዜ፥ የአማሌቅን ዝክረ ስሙን ከሰማይ በታች አጥፋው፤ ይህንን አትርሳ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 25: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in