YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘዳግም 26

26
1አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጥህ ምድር በገባህም ጊዜ፥ በወረስሃትም በኖርህባትም ጊዜ፥ 2አምላክህ እግዚአብሔር ከሚሰጥህ ምድር ከምትሰበስበው ፍሬ ሁሉ በኩራት ውሰድ በዕንቅብም አድርገው፥ አምላክህ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደ መረጠውም ስፍራ ይዘህ ሂድ። 3በዚያም ወራት ወደሚሆነው ካህን መጥተህ፦ እግዚአብሔር ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር እንደ ገባሁ ዛሬ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አስታውቃለሁ በለው። 4ካህኑም ዕንቅቡን ከእጅህ ወስዶ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠውያ ፊት ያኑረው። 5በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብለህ ተናገር፦ አባቴ የተቅበዘበዘ ሶርያዊ ነበረ፤ በቁጥር ጥቂት ሳለ ወደ ግብፅ ወረደ በዚያም ተቀመጠ፤ ታላቅ የሆነ የበረታም ቁጥሩም የበዛ ሕዝብ ሆነ። 6ግብፃውያንም ክፉ ነገር አደረጉብን፥ አስጨነቁንም፥ በላያችንም ጽኑ ከባድ ሥራን ጫኑብን፤ 7ወደ አባቶቻችንም አምላክ ወደ እግዚአብሔር ጮኽን፤ እግዚአብሔርም ድምፃችንን ሰማ፥ ጭንቀታችንንም ድካማችንንም ግፋችንንም አየ፤ 8እግዚአብሔርም በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በታላቅም ድንጋጤ፥ በተአምራትም፥ በድንቅም ከግብፅ አወጣን፤ 9ወደዚህም ስፍራ አገባን፥ ወተትና ማር የምታፈስሰውንም ይህችን ምድር ሰጠን። 10አሁንም እነሆ፥ አቤቱ፥ አንተ የሰጠኸኝን የምድሪቱን ፍሬ በኩራት አቅርቤአለሁ። አንተም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አኑረው፥ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ስገድ። 11አንተም በመካከልህም ያለ ሌዋዊና መጻተኛ አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተና ለቤትህ በሰጠው ቸርነት ሁሉ ደስ ይበላችሁ። 12አሥራት በምታወጣበት በሦስተኛው ዓመት የፍሬህን ሁሉ አሥራት አውጥተህ በፈጸምህ ጊዜ፥ በአገርህ ደጅ ውስጥ ይበሉ ዘንድ ይጠግቡም ዘንድ ለሌዋዊው ለመጻተኛውም ለድሀ አደጉም ለመበለቲቱም ስጣቸው። 13በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ በል፦ የተቀደሰውን ነገር ከቤቴ ወስጄ ለሌዋዊው ለመጻተኛውም ለድሀ አደጉም ለመበለቲቱም እንዳዘዝኽኝ ትእዛዝ ሁሉ ሰጥቼአለሁ፤ ትእዛዝህን ምንም አላፈረስሁም፥ አልረሳሁምም፤ 14በኅዘኔ ጊዜ እኔ ከእርሱ አልበላሁም፥ ለርኩስነቴም ከእርሱ አላወጣሁም፥ ከእርሱም አንዳች ለሞተ ሰው አልሰጠሁም፤ የአምላኬንም የእግዚአሔርን ቃል ሰምቼአለሁ፥ ያዘዝኽኝንም ሁሉ አድርጌአለሁ። 15ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማይ ጐብኝ፥ ሕዝብህንም እስራኤልን ለአባቶቻችን እንደ ማልህላቸው የሰጠኸንንም ወተትና ማር የምታፈስሰውን አገር ባርክ። 16አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ሥርዓትና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ዛሬ አዝዞሃል፤ አንተም በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ጠብቀው፥ አድርገውም። 17አንተ በመንገዱ ትሄድ ዘንድ፥ ሥርዓቱንና ትእዛዙን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ፥ ቃሉንም ትሰማ ዘንድ እግዚአብሔር እርሱ አምላክህ መሆኑን ዛሬ አስታውቀሃል። 18እግዚአብሔርም እንደ ሰጠህ ተስፋ ገንዘቡና ሕዝቡ መሆንህን፥ ትእዛዙንም ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥ 19ከፈጠራቸውም አሕዛብ ሁሉ በምስጋና በስም በክብር ከፍ ያደርግህ ዘንድ፥ እርሱም እንደ ተናገረ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ትሆን ዘንድ ዛሬ አስታውቆአል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in