ትንቢተ አሞጽ 7
7
1ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፥ እነሆም፥ የኋለኛው ሣር በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፥ እነሆም፥ ከንጉሡ አጨዳ በኋላ የበቀለ የገቦ ነበረ። 2የምድሩንም ሣር በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ እኔ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፥ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ። 3እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፥ ይህ አይሆንም፥ ይላል እግዚአብሔር።
4ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፥ እነሆም፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ፥ እርስዋም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች። 5እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድትተው እለምንሃለሁ፥ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ። 6እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፥ ይህ ደግሞ አይሆንም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
7እንዲህም አሳየኝ፥ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር። 8እግዚአብሔርም፦ አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም፦ ቱንቢ ነው አልሁ። ጌታም፦ እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ አደርጋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም፥ 9የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፥ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ አለ።
10-11የቤቴልም ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም ልኮ፦ አሞጽ፦ ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፥ እስራኤልም ከአገሩ ተማርኮ ይሄዳል ብሎአልና አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል ዐምፆብሃል፥ ምድሪቱም ቃሉን ሁሉ ልትሸከም አትችልም አለ። 12አሜስያስም አሞጽን፦ ባለ ራእዩ ሆይ፥ ሂድ ወደ ይሁዳም ምድር ሽሽ፥ በዚያም እንጀራን ብላ፥ 13በዚያም ትንቢትን ተናገር፥ ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ደግሞ ትንቢት አትናገር አለው።
14አሞጽም መልሶ አሜስያስን አለው፦ እኔ ላም ጠባቂና ወርካ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፥ 15እግዚአብሔርም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ እግዚአብሔርም፦ ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር አለኝ። 16አሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፥ አንተ፦ በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ ብለሃል፥ 17ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ምድርህም በገመድ ትከፈላለች፥ አንተም በረከሰች ምድር ትሞታለህ፥ እስራኤልም ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል።
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 7: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in